ቃና ዘገሊላ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ያደረገውን የበረከት ተአምር በየዓመቱ ጥር 12 ቀን በደማቅ ሁኔታ እንደምታከብር ይታወቃል፡፡
በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከበሩት የቃና ዘገሊላ በዓላት መካከል በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተከበረውን የቃና ዘገሊላ በዓል አስመልክቶ የበዓሉን ገጽታና ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የሰጡትን ቃለ ምዕዳን እና ትምርታዊ መልእክት ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ያደረገውን የመጀመሪያ ተአምር በማክበር ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ለበዓለ ጥምቀቱም ለበዓለ ቃና ዘገሊላም እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ ዓመታዊ በዓል በኢትዮጵያ በሰፊው የታወቀ በዓል ስለሆነ ሁላችንም አሁን እንዳደረግነው ለወደፊቱም በሰፊው ማክበር እንዳለብን የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ኃጢአታችንን ያስወገደበት ቀን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ አምላካዊ ሥራውን ሠርቶ አምላክነቱን የገለፀበት ዐቢይ በዓል ስለሆነ ሁላችንም ይህንን በዓል የማክበር ግዴታ አለብን፡፡ ወጣቶች ልጆቻችን የቤተክርስቲያናችን ልጆች ስለሆናችሁ ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ ምግባራችሁን አጽንታችሁ ቤተክርስቲያንን እንድትጠብቁ ቤተክርስቲያናችን አደራ ትላችሁአለች፡፡ ዛሬ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ውስጥ በምትገኘው ቃና በምትባለው መንደር ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠበት ዕለት ነው፡፡ ይኸውም በእመቤታችን ጠያቂነት ነው የተፈጸመው፡፡
ምክንያቱም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሠርግ ተጠርታ ስለነበር፣ ሐዋርያትም ተጠርተው ስለነበር የወይን ጠጃቸው አልቆባቸዋል እና አንድ ነገር አደርግላቸው አለችው፡፡ የልጇ በየጊዜው ተአምር ሲሠራ ታየዋለችና የሚአደርገውንም ተአምር በልቧ ትጠብቀው ነበር፡፡ ታሪክ እንደሚሠራ ታውቃለችና፤ ሠርገኞቹ ጠጅ አልቆባቸዋል ስትል ጠየቀችው፡፡ ጋኖቹን ሁሉ ውሃ ሙሉአቸው አለ ጌታ፡፡ በዚያ አካባቢ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩና እነዚያን ጋኖች ውሃ ሙሉባቸው ብሎ አዘዘ ውሃዎቹም በቅጽበት የወይን ጠጅ ሆኑ፡፡
ከዚያም ጋባዦቹም ተጋባዦቹም ተደነቁ የወይን ጠጅ ማለቁን ያውቁ ነበር እና. የወይን ጠጁም ከየት እንደመጣ አላወቁም ነበር፡፡ ኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደለወጠ አወቁ፡፡ ጋኖቹን ውሃ ሙሉ ብሎ ያዘዘም እርሱ ነውና፡፡ ስለዚህ ሁሉም የጌታችንን ተአምራት አደነቁ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ አቢይ ተአምር ነው፡፡ ይህ ተአምርም የተአምራቱ መጀመሪያ ነው፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠርቶአል፡፡ ሙታንን አስነስቷል፣ ድውያንን ፈውሷል፣ አንካሶች ቀና ብለው እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ ለምጻሞችን አንፅቷል፣ የዕውራንን ዐይን አብርቷል፡፡ ይህ ተአምር ግን የመጀመሪያ ተአምር ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ተአምር ታላቅ ተአምር ስለሆነ በየአመቱ በድምቀት እና በስፋት እናከብረዋለን ወጣት ልጆቻችንም ይህንነ የአባቶቻችሁን ፈለግ ተከትላችሁ ይህንን በዓል እናንተም ልጆቻችሁም የልጅ ልጆቻችሁም እንዲአከብሩት ለልጆቻችሁ ማስተላለፍ ይገባችኋል፡፡
ይህንን በዓል በመልከኡ ስም የምናከብረው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በተራዳኢነቱ፣ በጠባቂነቱ፣ በሊቀ መላእክትነቱ፣ ለእግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ በእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀናል፣ የማልደናል፣ ብለን ነው የምናከብረው፡፡ የሌሎች ቅዱሳን መላእክትን የሰማዕታትን የጻድቃንን በዓል የምናከብረው በማላጅነታቸው በተራዳኢነታቸው ያማልዱናል ብለን ነው፡፡
ስለዚህ ይህ በዓል ለሁላችንም ክብር ስለሆነ በክብር ላይ ክብርን የሚአሰገኝ ስለሆነ ይህን ዐቢይ በዓል በድምቀት እና በስፋት እናከብረዋለን፡፡
ይህንን በዓል በተለየ ሁኔታ የምታከብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የውጭ ጋዜጠኞችም ጎብኚዎችም የሚመሠክሩት ይህንኑ ነው፡፡ አንድ የውጭ ጎብኚ ሲናገር እንደሰማነው አንድ መቶ ሰላሳ ሀገሮችን ጎብኞቼአለሁ እንደ ኢትዮጵያ ያለ የበዓል አከባበር አይቼ አላውቅም ብሏል፡፡ ይህ ትልቅ ምስክርነት ነው፡፡
ይህን የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚአደርገው የመስቀል በዓል በዩኒስኮ መመዝገቡ ነው ይህ ታላቅ ክብር ነው፣ ይህም ምዝገባ ለበዓለ ጥምቀትም ለቃና ዘገሊላ በዓልም ፤ ይህንን ዕድል እንድናገኝ ደማቅ በሆነ ጉባኤ ደማቅ በሆነ አክብሮት ደማቅ በሆነ የአምልኮ ተግባር ስለምናከብረው ነው በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ የተደረገው፡፡
ስለዚህ ክርስቲያኖች ሃይማኖታችሁን ጠብቁ፣ ባሕላችሁን አክብሩ እናንተ በሀገራችሁ ኩሩ ወጣቶች እባካችሁ ችግር ወዳለበት ወደ ባዕድ ሀገር አትሂዱ ክብራችሁን ጠብቁ፡፡ ወጥታችሁ ወርዳችሁ ጥራችሁ ግራችሁ ኑሮአችሁን አሸንፉ ከአሁን ቀደም ያያችሁት እና ያየነው ትልቅ ትምህርት ነው ያየነው፡፡ ወደ አረብ ሀገሮች ሂደው፣ ተሰደው ብዙ ሥራ ሠርተው የሰበሰቡትን ገንዘብ እንኳን አላገኙም ከመብት መብት የላቸውም፡፡ ለገንዘባቸው መብት የላቸውም ለሕይወታቸው ዋስትና ላቸውም፡፡ እምነታቸውን
ለመግለጽ ዋስትና የላቸውም በጠቅላላ ለሕይወታቸው ዋስትና የላቸውም፡፡ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው መከራ የሚያሳዝን ቢሆንም ነገር ግን ከነሕይወታቸው ተመልሰዋል፣ የደከሙበት ገንዘባቸው ግን ተዘርፎ ቀርቷል፡፡
ዳኛ የሌለበት ፍትሕ ርትዕ የሌለበት ሀገር ሂደታችሁ እንደዚህ አይነት ውርደት ከሚደርስባቸው በሀገራችሁ ተከብራችሁ ኑሩ፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ይህ ንፁሕ አየር እንኳን በሌላው ዓለም የለም፡፡ ይህ ንፁሕ አየር የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ነው፤ ዋጋ ያልከፈልንበት ደጅ የማንጠናበት ንጹሕ አየር በሌላው ዓለም የለም፡፡ ንፁሕ አየር እየተነፈስን ይህችን ለልማት የተዘጋጀች ሀገር አልምተን ሀብታችንን በዚህ እንደምናገኝ ሁላችንም ልናውቅ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ፀጋ ስለሰጠን እናመሰግናለን፡፡
የጥምቀቱም በዓል ሆነ የቃና ዘገሊላ በዓል የሰመረ በዓል እንዲሆን፣ አንድነቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የሀገራችን ወታደሮች የፓሊስ ሠራዊት እና የመንግሥት ባለስልጣናት ሁሉ ይህን በዓል ለማክበር ጥበቃ ስለአደረጉልን በጣም እናመሰግናለን፡፡ ቤተክርስቲናችንም ታመሰግናለች፡፡ አሁንም ቢሆን ሁላችንም ለሰላም እንሰለፍ በመንፈሳዊም ይሁን በሥጋዊ ተቋማት ሀገርን የሚረብሽ ሀብት የሚረብሽ ሁከት የሚያስነሳ መታየት የለበትም፡፡ ይህ ኃላፊነት የሁሉም ቢሆንም እንኳን ክርስቲያኖች ግን የእግዚአብሔር ልጆች ነን የሰላም ልጆች ነን፣ የአንድነት ልጆች ነን ስለዚህ ሀገራችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ህልውናችንን መጠበቅ አለብን እግዚአብሔርን ማክበር አለብን፡፡ ስለዚህ በዚሁ ጸንተን እንድንኖር ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ዛሬ በዚህ ቦታ ተገኝተን ይህንን ታላቅ በዓል ለማክበር ስለበቃን አምላካችን የተመሰገነ ይሁን በማለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ታቦቱ በሚጓዙበት ጉዳና ላይ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በማያያዝም በወጣቶች እጅ ተይዘው የቆዩትን ርግቦች ቅዱስነታቸው እንዲለቁአቸው የተደረገ ሲሆን ከተለቀቁት ርግቦች መካከል አንዱ ጥቁር አንዱ ነጭ ርግብ ሲሆኑ ጽላቱን በተሸከሙ ካህናት ላይ በጽላቱ ተቀምጠው ታቦታቱ ቤተ መቅደሱ እስከሚገቡ ድረስ ርግቦቹ በጽላቱ ላይ ተቀምጠው ተጉዘዋል፡፡
በዚህም አስደናቂ ተእይንት ምዕመናን በታላቅ ዕልልታ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ታቦታቱ በቤተክርስርስቲያኑ አጠገብ ከደረሱ በኋላ ለከተወሰኑ ደቂቃዎች በመዘምራን ያሬዳዊ ወረብ የቀረበ ሲሆን ከዚሁ ጋር በማያያዝ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንጂ እና ማጂ አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚከተለውን ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ ግበሩ በዓለ በትፍስሕት
ይህ ቃል ነቢዩ ዳዊት የተናገረው ቃል ነው (መዝ. 117) አሁን የያዘነው ወራት ዘመነ አስተርእዮ ዘመነ አንሶስወ ይባላል፡፡
አስተርእዮ ማለት እኔን እንደምታዩኝ በጊዜው እና በሰዓቱ የነበሩ ሰዎች አባቶቻችን ሐዋርትም ሌሎቹም እግዚአብሔር የፈቀደላቸው እግዚአብሔርን ባጭሩ ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ መልኩንም አይተውታል፣ ትምህርቱንም ሰምተውታል፡፡ ዛሬ በሥጋ የተገለጠበት በዮርዳኖስ ወንዝ የታየበት ዕለት ነው፡፡ የአይሁድ ጥምቀት አለ የዮሐንስም ጥምቀት አለ፣ ሁሉም ጠቃሚ አይደለምና ጠቃሚ የሆነው ክርስትና ያለው ጥምቀት ማያትን ቀድሶ የሰጠን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮሐንስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ጎዙውን የቀጠለበት ዕለት ነው፡፡ በዓሉ የውኃ በዓል ስለሆነ ከጥምቀት ጋር አብሮ ተደርጎ ነው እንጂ የቃና ዘገሊላ በዓል የካቲት 23 ቀን ነው፡፡
አመሳልስት ዕለት የሚለው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኃላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ነው የሄደው፡፡
ከዚያም አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ከማንም ጋር አልተገናኘም፡፡ ሰይጣንም ሊፈትነው ቀርቧል፡፡ አምላክ ስለሆነ በአምላክነቱ ኃይል አሸንፎታል፡፡ እግዚአብሔር እዚያ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ከጾመ በኃላ ነው ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ የሄደው፡፡ ሱባኤውን ጨርሶ ከሐዋርያት እና ከእናቱ ጋር ተገናኝቶ እነሱን አጽናንቶ ሰላም ብሎ ከእነሱ ጋር ሆኖ ነው ማክሰኞ ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ የሄደው፡፡ አመሳልስት ዕለት የሚለው ለአርባ ቀን ነው፡፡ ታሪክ በኢየሩሳሌም ትምህርት በኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢየሩሳሌም የተሠራው ታሪክ የተደረገው ትሩፋት የተጸለየው ጸሎት እግዚአብሔር የሠራው ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ ነው እንጂ የሚደነቀው አይሁዶችማ አልተቀበሉትም የልጅነት ጥምቀት አላገኙም፡፡ ዮሐንስ ከእኔ በኃላ የሚመጣው የጸና ነው እሱ በእሳት እና በውኃ ያጠምቃችኃል ብሎ ተናግሯል፡፡ እሳት የበላው መሬት ለተክልም ለእህልም ይመቻል፡፡ ዛሬ ማዳበሪያ መጥቶ መሬቱን በሽተኛ አደረገው እንጂ የሀገራችን መሬት ራሱ ቅጠሉ የሚያርፍበት እርሻው ሲታረስ ለመሬቱ ማዳበሪያ ይሆናል፡፡
በእሳትና በውኃ ያጠምቃችኋል ከእኔ በኃላ ይመጣል፡፡ የጫማውን ጠፍር እንኳን ልፍታ የማይገባኝ እሱ በመንፈስ ቅዱስም በውኃም ያጠምቃችኃል ብሎ ተናግሯል፡፡ የልጅነት ጥምቀት ያገኘነው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያገኘንበት ቤተክርስቲያንም አምና የተቀበለችው የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ነው፡፡ በጥምቀት ሰላም ተመሥርቷል፤ መለያየትም ጠፍቷል፤ የጥል ግድግዳ ተንዱአል፡፡ የወደቁት ተነስተዋል፣ የተሰደዱት ተመልሰዋል፣ የተራቡት ጠግበዋል፣ ያጡት አግኝተዋል፣ የተራቆቱት ለብሰዋል፣ ጌታችን እና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሠርጉ ቤት ተጠርቷል የሠርጉም ቤት ባለቤት ያየውን ሁሉ ጠርቶ ጠርቶ አፍሮ ነበርና መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጨነቀውን ሁሉ ይረዳልና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ አማካኝነት የሠርጉ ቤት ባለቤት ከውርደት ድኗል፣ ውሃውም ወደ ወይን ጠጅ ተለውጧል፡፡ ዘይሴኒ ወይነ አስተደሀርከ ሰው ሁሉ ተራውን ጠጅ ያመጣል አንተ ግን መልካሙን ጠጅ እስከ አሁን አቆየህ ተብሎአል ያ የሠርጉ ባለቤት ጥኢሞ አንከረ ሊቀ ምርፋቅ ማየ ዘኮነ ወይነ ቃና ጌታ በተጠመቀበት አካባቢ ትገኛለች ብዙም ሩቅ አይደለችም፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ውሃውን የባረከበት እኛን የቀደሰበት ዕለት በመሆኑ ሁላችንም ተሰብስበናልና ይህንን በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡት ሁሉ ቅዱስ አባታችን ቡራኬአቸውን እና ትምህርታቸውን ይሰጡናል በማለት ብፁዕነታቸው ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
በማያያዝም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመጨረሻው ጸሎት እና ቡራኬ ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡
{flike}{plusone}