ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ.ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የ2017 ዓ/ም የጾመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል። መግለጫው የሚከተለው ነው።
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ፡-
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን፤
በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-
የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም ኣደረሳችሁ!
‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፣ ነፍሴ እግዚአብሔርን እጅግ ታከብረዋለች›› (ሉቃ.፩÷፵፮)፤
ይህንን ዐረፍተ ነገር የተናገረችው ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በሰራው ስራ ሰውነታችንን ለመዋሓድ የመረጣት ምርጥ የፍጥረት ወገን ናት፤ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጥሮኣል፤የእግዚአብሔርም ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መመረጥም በእግዚአብሔር ለሰው የተደረገ ምርጫ ነው፤
የሰው መዳን ከጥንቱ ከጠዋቱ በእግዚአብሔር ልዩ ኣሰራር እንደሚከናወን በነቢያት የተገለጸ ነበረ፣‹‹ኣኮ በተንባል ወኣኮ በመልኣክ ኣላ ለሊሁ እግዚእ ይመጽእ ወያድኅነነ፤ በኣማላጅም ኣይደለም፤ በመልኣክም ኣይደለም እሱ ራሱ ጌታ መጥቶ ያድነናል እንጂ›› የሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ትንቢትም ይህንን ያስረዳል፤ ቃለ ትንቢቱ ድኅነታችን በጌታ ቤዛነት እንደሚከናወን ያረጋግጣል፤ይህም ሊሆን የቻለው ከፍጡራን ወገን በደሙ ቤዛነት ፍጡራንን የሚያድን ስለሌለ ነው፤
ከዚህ ኣንጻር የሰው መዳን በእግዚአብሔር ኣሰራር በደም ቤዛነት ከሆነ፣ በደሙ ቤዛነትም ዓለምን ማዳን የሚችል ከፍጡር ወገን ከሌለ፣ መዳናችን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር እጅ ብቻ የተንጠለጠለ ነበረ፤ እግዚአብሔር በደሙ ቤዛ ሆኖ ዓለምን ለማዳን ደግሞ ደም ሊኖረው ይገባ ነበር፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በክዋኔው ደም የሌለው ስለሆነ ለቤዛ ዓለም የሚፈስ ደምን ገንዘብ ማድረግ ነበረበት፤ይህንን ደም ለመዋሓድ ቅድስት ድንግል ማርያምን መረጠ፤ ለዚህ ብቁ እንድትሆንም በእስዋ ላይ ስራውን ሰራ፤በምርጫውም መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ደማዊ ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ለቤዛዊ መሥዋዕት መንገዱን ኣመቻቸ፤
ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት መሰላል ለመሆን በእግዚአብሔር የተመረጠች በመሆኗ ኣንቀጸ ኣድኅኖ ወይም የድኅነት በር ትባላለች፤ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ ታላቅ ነገረ ድኅነት መመረጥዋ እጅግ ታላቅ ዕድል መሆኑን ስለተገነዘበች ‹‹ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልኛልና›› በማለት እግዚአብሔርን በመዝሙር ኣመስግናለች ኣክብራለችም፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና እና የኣምልኮ መዝሙር የኛም መዝሙር ነው፤ እግዚአብሔር ለቅድስት ድንግል ማርያም ታላላቅ ስራዎችን እንደሰራ ለኛም ብዙ ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልናል፤ እየሰራልንም ነው፤ ለሰራልን ኣምላክም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ክብርን መስጠት ይገባናል፤ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ክብርም በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ሊሆን ይገባል፤ የድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሕይወት በማስተዋል በትሕትና፣ በትዕግሥት በርኅራኄ በመታዘዝ በንጽህና በቅድስና በክብርና በበረከት የተሞላ እንደሆነ በቅዱስ መጽሓፍ ከተጻፈው ሥነ-ሕይወቷ መረዳት እንችላለን፤
ታድያ በእርሷ ክብርና ተማሕፅኖ የምንተማመን ልጆቿም የእሷን ያህል እንኳ ባንችል ወደእርስዋ የሚጠጋጋ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፤ ይህም የምናደርገው ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ መዳን ሲባል ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስናከብር እንከብራለን እንድንማለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር የማንሰጥ ከሆነ ግን ውጤቱ መክበር ሳይሆን ሌላ ነው የሚሆነው፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው፤ ጾም የኃጢኣት መግቻ መሳሪያ በመሆኑ ‹‹ልጓመ ኃጢኣት›› ተብሎ ይታወቃል፤ በዚህም ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢኣት ከሚያጋግሉ ምግቦች ኣርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን፤
የጾም ጥቅም ከጥንት ጀምሮ የታወቀ በእግዚአብሔርና በሰውም ተቀባይነት ያለው ነው፤ እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል፤ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‹‹እንዳልኸኝ ይሁንልኝ›› ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደእስዋ ታዛዥ መሆን አለብን፤
ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም ኣይስተውም፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሳሪያ ኣያመርትም ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንድምህን እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ ኣለ እንጂ ግደል ብሎ ኣላዘዘምና ነው፤ኣሁንም በዚህ ባለንበት ዓለም በጣም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው ኣስከፊ መሆኑ ኣይቀርም ፤
ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት ‹‹በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር›› የሚል ነው፤ ‹‹ፍትሕና ርትዕም ለሰው ልጅ መነፈግ የበለትም፤ ሰው በምድር ላይ ሰርቶ የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ይህንን ማድረግ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ነው፤ስለሆነም ለእግዚአብሔር ክብርና ለራሳችን መዳን ስንል ለእርሱ በመታዘዝ በሕይወትና በሰላም እንኑር፡፡
በመጨረሻም፡-
በጾመ ማርያም ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እንድናሳልፍ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናስተላልፋለን፤
መልካም የሱባዔ ወቅት ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲሲ
©የኢኦተቤ ሕዝብ ግነኙነት መምሪያ