ሰንበት ት/ቤት – ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ታሪክ የወጣቶች ሰንበት ት/ቤት ማቋቋም የተጀመረው ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ የኸውም ከብዙ ዓመታት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሃይማኖት ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ወጣቶች “የሥላሴ ማህበር” ተብሎ የሚጠራ አንድ ማህበር መሠረቱ፣ ይህ ማህበር ለወንዶች ብቻ የተቋቋመ ነበር ይሁንና ከጥቂት ዓመታት በኋላ የካቴድራሉ አስተዳደር ወጣት ልጃገረዶችም የራሳቸውን ማህበር መመሥረት እንዳለባቸው አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ለጸሎትና ለአምልኮ ወደ ካቴድራሉ የሚመጡ ልጃገረዶችን ሰብስቦ እነርሱም የራሳቸውን ማህበር እንዲያቋቁሙ አበረታታቸው በመሆኑም “ማህበረ ክርስቶስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ማህበር መሠረቱ፡፡

የእነዚህ ማህበር አባላት የተሻለ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርት ማግኘት ሲጀምሩ የቤተክርስቲያንን ትምህርት እየተማሩና እያወቁ በመምጣታቸው በተለይም ልጃገረዶች የቤተክርስቲያንን ዜማ በማጥናት በቤ/ክ ውስጥ ከቁርባን በኋላ መዘመር ጀመሩ፡፡ ይህም እንደ አዲስ ክስተት ታይቶ በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ የሚወደድ ሆኖ ተገኘ የእነዚህ ማህበራት ዓላማቸውም የሚከተሉት ነበሩ፡-

  1. የክርስትና ሃማኖትን መሰረታዊ ዓላማዎች መማርና ማስተባበር ፣
  2. ሰብአዊ ተግባራትን ማካሄድ፣
  3. የክርስቲያንን ብሔራዊ ባህል መጠበቅ፣
  4. ወጣት ልጃገረዶች ያለፍርሃት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ለህበረተሰቡ አገልግሎት የሚስፈልገውን የሥራ አመራር ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ናቸው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቅዳሴ ጊዜ የወጣት ልጃገረዶች ተሰጥዎ መቀበልና ከቅዳሴም በኋላ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን ማስማታቸው እንደ አዲስ ነገር በመታየቱ ተግባሩ በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች ቀጥሎ ተስፋፍቷል፡፡

የምስካየ ኅዙናን ቤተክርስቲያን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት የተፈሪ መኮንን እና የእቴጌ መነን ት/ቤት ተማሪዎችን በብዛት መሳብ በመቻሉ በየሳምንቱ እሑድ ተማሪዎች በብዛት ወደ ቤ/ክ እየመጡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተሳታፊ ከሆኑ በኋላ ብዙዎች በቤ/ክ እንዳንድ ሥራዎች በፈቃደኝነት መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተማሪዎችና በገዳሙ መካከል አንድነትን መፍጠር የሚችልና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥበት ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም ወጣቶቹ በመጠየቃቸው  “ተምሮ ማሰተማር” የተባለው ታዋቂው ሰንበት ት/ቤት በ1939 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡

የተምሮ ማሰተማር ማህበር ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ለማህበሩ አባላትና ለህብረተሰቡ አስፈላጊ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚያ በመቀጠል በ1942 ዓ.ም የተቋቋመው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲሆን የወንጌል መልዕክተኞችና የእሑድ ት/ቤት ማህበር ተመሠረተ፣ በዚሁ ጊዜም ነበር የአሥመራው ማህበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት ማህበር የተቋቋመው፡፡

ቀጥሎም ወደ ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያምና መንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል፣ ወደ ገነተ ጽጌ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስና ወደ ሌሎች የአዲስ አበባ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት ተስፋፋ ከዚያም አልፎ ወደ ዋና ዋና (በጊዜው አጠራር ጠቅላይ ግዛት) ከተሞችና ታላላቅ አውራጃዎች የተቋቋሙበት የደብሩን መለያ ስም በመያዝ በልዩ ልዩ የቅጽል ስም የወጣቶች መንፈሳዊያን ማህበራት እየተባሉ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ተጓዙ፡፡ የአሁኑ ሰንበት ት/ቤት የወጣቶች መንፈሳዊ ማህበር የቀድሞ አመሠራረቱ ከላይ እንደተጠቀሰው በወጣቶችና ልጃገረዶች ግላዊ ተነሳሽነት ፤በብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአንዳንድ ዓላማው በገባቸው የአድባራት አለቆችና ሰባክያነ ወንጌል በጎ ፈቃድና ድጋፍ ነበር፡፡ 

በተለይም በ1936 ዓ.ም በወቅቱ የመንበረ ጸባኦት ቅዱስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ የመጀመሪው ሊቀሥልጣናት ሆነው የተሾሙት ሊቀ ሥልናናት አባ መልዕክቱ በኋላም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ ተብለው የተሸሙት ማህበሩ እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ ማህበሩ በአገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ትልቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ማህበራት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ቀስ በቀስ በሁሉም ገዳማትና አድባራት ተቋቁሞ ስለነበር ከቤተ ክህነቱ ጋር የሚያገኛኘው መስመር የግድ ስለነበር በጊዜው በስብከተ ወንጌልና ማስታወቂያ መምሪያ ስር የወጣቶች መንፈሳዊ ማህበራት አንድነት ማእከላዊ ጽ/ቤት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተቋቁሞለት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ይህ ማዕካላዊ ጽ/ቤት እስከ 1965 ዓ.ም ድረስ በመጠኑም ቢሆን የወጣቶች መንፈሳዊያን ማህበራትን ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡ ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ግን ወደ ወጣቶች ጉዳይ መምሪያነት አደገ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለም በ1966 ዓ.ም  በመላው አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የተቋቋሙት የወጣቶች መንፈሳውያን ማህበራት የለውጡን ሂደት ተጠቅመው በራሳቸው ውሳኔ አጠቃላይ ጉባኤን መሰረቱ ይህ የወጣቶች መንፈሳውን ማህበራት አጠቃላይ ጉባኤ በዚያ ክፉ የደርግ ዘመን በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ እጅግ ብዙ ቁም ነገሮችን ለቤተ ክርስቲያኒቷ በቆረጥነት አበርክቷል መምሪያውንም ያጠናከረው አጠቃላይ ጉባኤው ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤውና በመምሪያው የተጠናከረ ትብብር የአሁኑ ሰንበት ት/ቤት እንደቀድሞው የወጣቶች መንፈሳዊ ማህበር እየተባለ በ1970 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዓዋዲ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህጋዊ አካልነቱ ተረጋግጦ ሙሉ በሙሉ ዐውቅና አገኘ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ስያሜው ቀጥሎ በመላ ኢትዮጵያ በስፋት ተስፋፋ፡፡

ይሁን እንጂ ከ1974 ዓ.ም ካቲት ወር ጀምሮ የደርግ  መንግስት “ከአኢወማ” ጋር በስም ይሞካሻል፣ ይመሳሰላል ብሎ በውስጥ በደረገው ተጽዕኖ ምክንያት ሁሉም የወጣቶች መንፈሳውያን ማህበራት በቅዱሳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ብልህነት የተመላው ውሳኔ ነበሩ ስማቸው ተለውጦ ይኸውና ከዕለቱ በመነሳት የሰንበት ት/ቤት ተብሎ እስከ አሁን ሊደርስ ችሏል፡፡ መምሪያውም የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የተባለው ከዚያን ወዲህ ጀምሮ ነው፡፡