ሰላም በምድር

                                “ሰላም በምድር”
የዓለም መድኃኒትና የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ሌሊት ሰማያውያን ሠራዊትና ምድራውያን ሰዎች በአንድ ላይ የዘመሩት መዝሙር “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” የሚል ነው፡፡
ይህም የምሥራች ቃል ትርጓሜው “ምስጋና ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ ይሁን” ማለት ነው፡፡ (ሉቃ. 2÷14)፡፡ ይህ ቃል የሰላምን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ሰላም ለሰዎች ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ላለ ማንኛውም ፍጡር እጅግ አስፈላጊውና የደህንነቱም ዋስትና እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ “ሰማያት ስሙ! ምድርም አድምጪ!” በማለት በሰማይና በምድር እያማፀነ የተናገረው ቃል ትልቅና ትንሽ፤ የበላይና የበታች የሚል ትርጉም ያለውና በጊዜው በነበረው ኅብረተሰብ መካከል የነበረውን የኑሮ ልዩነት ለመግለጥ የተጠቀመበት ቃል ሲሆን፡ – ዋናው መልእክት ግን ሰውነታችሁን አንጹ፣ ክፉ ማድረግን ተው፤ መልካም መሥራትን ተማር …” በማለት ትልቅ፣ ትንሽ ሳይባል የሰው ልጆች ሁሉ በመካከላቸው ያለውን ፀብና ጭቅጭቅን፣ ሰላም ማጣትንና እርስ በርስ መለያየትን፣ በጠቅላላ ክፉ ማድረግን ትተው ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ (ኢሳ. 1÷2፣16-17)
ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ ምኞትና ፍላጎት ቢሆንም ነቢዩ ኢሳይያስ እሱ በነበረበት ዘመን በነበረው ኅብረተሰብ መካከል ፀብና ጭቅጭቅ፤ አለመግባባትና ንትርክ፣ እርስ በርስም መለያት በዝቶ፣ ሰላም ታጥቶ የነበረበት ጊዜ ሆኖ በማየቱ ሰዎች ሁሉ ፀረ ሰላም የሆነውን ክፉ ሥራቸውን ትተው በሰላምና በፍቅር መኖር እንዲችሉ ቃሉን አሰምቶ “በሰማይና በምድር እየተማፀነ ስለ ሰላም ካስተማራቸው በኋላም ሰዎች ሁሉ ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ፤ ጦራቸውንም ማጭድ እንዲያደርጉና ፊታቸውን ወደ ልማት መልሰው አገር እንዲያለሙ በአጽንዖት ነግሮአቸዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንደማይነሣና ሰልፍም እንደማይኖር፤ ይልቁንም “አለቅነቱ በጫንቃው ላይ የሆነ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ” ተብሎ የሚጠራ አንድ ሕፃን እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሮላቸዋል (ኢሳ. 9÷6)፡፡
የዘመኑ ፍጻሜም ሲደርስ በነቢዩ ኢሳይያስና በሌሎቹም ነቢያት ትንቢት የተነገረለትና ሱባዔም የተቆጠረለት ያ ሕፃን ከቅድስተ ቅዱሳን፣ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ የይሁዳ ምድር በምትሆን በቤተልሔም ተወለደ፡፡
“የይሁዳ ምድር የመትሆኚ አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ ነገሥታት ከቶ አታንሽም ሕዝቤ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና” ተብሎ አስቀድሞ በነቢዩ ሚክያስ ትንቢት ተነግሮ ነበርና (ሚክ. 5÷2)፡፡
ጌታችን በተወለደ ጊዜ “ሰላም በምድር” የሚል የምሥራች ድምፅ በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሰማቱ በይሁዳ ምድር ቤተልሔም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግርግጥም “እውነተኛ አምላክና የሰላም አለቃ” ተብሎ የተገነረለት እርሱ እራሱ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የተረጋገጠና የታወቀ ሆነ፡፡
እሱም በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት እንደተነገረው ሁሉን የሚችል እውነተኛ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ዕለቱን ልደግ፤ ልመንደግ፣ ወደዚህዓለም የመጣሁበትንም ዓላማ ወዲያውኑ ላድርግ ሳይል አምላክ ቢሆንም አርአያ ሰብእን የነሳ እውነተኛ ሰውም በመሆኑ ቀስ በቀስ አድጎ ከ30 ዓመት በኋላ የሰላም መሠረት የሆነውን ወንጌል በሚያስተምርበት ጊዜ “ሌሎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም ለሌላው አድርጉ፡፡ ሌላው በእናንተ ላይ ሊያደርግባችሁ የማትፈልጉትን እናንተም ደግሞ በሌላው ላይ አታድርጉ፡፡” በማለት የሰላም መሠረት የሆነውን ወርቃማ ሕግ መሥርቶአል፡፡ “የሰላም አለቃ” እንደመሆኑም መጠን “ሰላም ለኲልክሙ” (ሰላም ለሁላችሁ ይሁን)፤ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ”፤ “ሰላምን እተውላችኋላሁ” በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምን ተመኝቶላቸዋል፡፡ ሰላምን በተመለከተም ብዙ አስተምሮአቸዋል (ዮሐ. 14÷27፤ 20÷19-23)፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም የኢየሱስ ክርስቶስን የሰላም ዓላማ በመከተል እሱ ያስተማረውንና የሰበከውን የሰላም ወንጌል በየጊዜው እየሰበከች ትገኛለች፡፡ ማስተማርና መስበክ ብቻም ሳይሆን ሁል ጊዜ ስለሀገር ብሎም ስለዓለም ሰላም አጥብቃ ትጸልያለች፡፡ እንዲያውም የምሥጢራት ሁሉ ማጠቃለያና መደምደሚያ በሆነው ጸሎተ ቅዳሴዋ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ስለሀገር ብሎም ስለዓለም ሰላም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ ትጸልያለች፡፡ የቅዳሴዋ ዋና አዝማች ሰላም ስለሆነ ዲያቆኑ “ተንሥኡ ለጸሎት” ሲል ካህኑ (ቄሱ) ደግሞ “ሰላም ለኲልክሙ” እያለ ክርስቶስ የሰበከውን ሰላም በቅዳሴው ጊዜ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይሰብካል፡፡ ሕዝቡም “አሜን እንደቃልህ ይደረግልን” በማለት ተሰጥዎውን ይመልሳል፡፡ ስለሰላም ያለውን በጎ ምኞት እየገለጠ ልመናውንና ምስጋናውን ለፈጣሪው ያቀርባል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ግን በዓለም ላይ የሰላም ድምፅ እያነሰ፣ የሽብርና የጦርነት ሁኔታ እየበረከተ መታየቱ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ የዓለም ሕዝብ ስለሰላም ያለው ደንታቢስነት የሚያመለክትና የሚያረጋግጥም ሆኗል፡፡
“ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ (በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሰላምን አደረገ)” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ በክርስቶስ ደም ፈርሶና ፈጽሞም ተደመስሶ ይጠበቅ የነበረው ሰላም ተግባራዊ ሆኖ ሳለ በሰዎችና በሰዎች መካከል ግን የሰላም ጉዳይ ከቃል አልፎ ተግባራዊ ባለመሆኑ በተቃራኒው ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እየተነሳ በየሀገሩ በሚደረጉ ጦርነቶችና የሽብር ሂደቶች መላው ዓለም እየተናወጠና እየተናጠ በታላቅ ችግር ላይ በመገኘቱ መሣሪያ ያልታጠቀው ሲቪል ሕዝብ ጭምር የፈንጂና የጥይት ሰለባ እየሆነ ይገኛል፡፡
ይህም በመሆኑ የዓለም ኅብረተሰብ በሙሉ ከሰላም ይልቅ የጦርነትን ወሬ መስማት ግዴታ ሆኖበታል፡፡ ከጦርነትም በላይ አጥፍቶ የመጥፋትና የሽብር እንዲሁም የዋይታና የሰቆቃው ድምፅ ባየለበትና ባልተረጋጋች ዓለም ውስጥ እየኖረ ይገኛል፡፡ ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ ኃያላን መንግሥታት የሚመሯቸው ታላላቅ አገሮች ሳይቀሩ ሕዝባቸው በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደቤቱ መግባት በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ት/ቤቶች፣ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና የእስፖርት ሜዳዎች ሁሉ ከሥጋት ነፃ ባለመሆናቸው ሕፃናት ሳይቀሩ ወላጆቻቸውም ጭምር ከፍርሃት የተነሣ እየተሸማቀቁ የሚኖሩባት አስቸጋሪ የሆነች ዓለም ሰዎች በራሳቸው በመፍጠሯቸው ሁኔታቾች ሁሉ በጣም የሚያሳቅቁ ሆነዋል፡፡
እጅግ የሚገርመው ግን በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች እያዳንዳቸው በሚገናኙባቸው ጊዜያት ሁሉ እርስ በርሳቸው “ሰላም ሰላም” በመባባል የሰላምታ ቃል ይለዋወጣሉ፣ እጅ ለእጅም ይጨባበጣሉ፡፡
በተለይም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ ሰዎችና መላእክት በአንድ ላይ የዘመሩትን የሰላም መዝሙር ከመዘመር ጋር “ሰላም በምድር” የሚለውን መልእክት ለመላው ኅብረተሰብ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡ “ሰላምን ፈልጋት፣ ተከተላትም” ተብሎ እንደተጻፈ እያንዳንዱ ኅብረተሰብ የዘር፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነቶችን  በማስወገድ ከሁሉም በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡
 ( ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘው)

{flike}{plusone}