ርዕሰ ዓውደ ዓመት የአዲስ ዘመን መጀመሪያ

በኢትዮጵያ ያለፈው ዓመት አልቆ የሚተካው የሚጀመርበት መስከረም አንድ ቀን ስለሆነ በቤተክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት ርዕሰ ዓውደ ዓመት ይባላል፡፡ ዘመን ሲያልፍ ዘመን ይተካል፡፡ ትውልድም ሲያልፍ ትውልድ ይተካል፡፡ ለኅልፈትና ለውላጤ የተፈጠረ ፍጡር ሁሉ ወቅትና ጊዜ አለው፡፡ በዚያው በተሰጠው ዘመን ሁሉም ሥራውን ያከናውናል አከናውኖም ያልፋል ያለሥራ የተፈጠረ ፍጡር የለምና፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን ፈጥሮ ሲፈጽም “ወርእየ እግዚአብሔር ኵሎ ዘገብረ ከመ ጥቀ ሠናይ” (እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ መልካም እነደሆነ አየ) ይላል /ዘፍ.1÷31/ ይህም የሚያስረዳው የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ያለ አገልግሎት የተፈጠረ አለመሆኑን ነው፡፡

በሰው ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጡራን መካከል የሚወደዱና የሚጠሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉም ፍጥረታት የተወደዱ ናቸው፡፡ ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “እግዚአብሔር የፈጠረው ሥነ-ፍጥረት ሁሉ ያማረና የተወደደ ነው ምንም የሚጣል የለውም ብሏል” /1ኛ.ጢሞ.4÷4/

እግዚአብሔር ፈጥሮ አይጥልም፣ አይረሳም፣ አይዘነጋምም ፍጥረቱን ሁሉ በመግቦቱ ተንከባክቦ ጠብቆ እስከ ወሰነለት ጊዜ ያኖረዋል፡፡ በይበልጥ ለሰው የሚያደርገው ልግስና የሚሰጠው ጸጋ፣ ጥበብ ከሌላው ፍጥረት በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

በምግብ በልብስ እንዳይቸገር ከማድረጉም ሌላ ዘመኑን የሚሰፍርበትና የሚቆጥርበትም አዘጋጅቶ እንዲጠቀም ማስተዋልን ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ሰከንዱን በደቂቃ፤ ደቂቃውን በሰዓት፤ ሰዓቱን በቀን፤ ቀኑን በሳምንት፣ ሳምንቱንም በወር፣ ወሩን በዓመት እያጠቃለለ ምድራዊ ሕይወቱን ከማገባደድ ይደርሳል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከላይ እንተገለጸው አንዱ ዓመት አልፎ ሌላው ሲተካ ርዕሰ ዓውደ ዓመት የዓመት መጀመሪያ ይባላል፡፡

በኢትዮጵያ የዘመን አመዳደብ ዘመናቱ አራቱን ክፍላተ ወንጌል በጻፉት በአራቱ ወንጌላውያን ስም እንዲጠሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ወስነዋል፡፡ ወንጌላውያኑም ማቴዎስ ማርቆስ ሉቃስና ዮሐንስ ናቸው፡፡ ከእነርሱም ማቴዎስና ዮሐንስ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ሲሆኑ ማርቆስና ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ናቸው፡፡

በኢትዮጵያችን የዓመቱ መጀመሪያ የሚጠራው ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ነው፡፡ ወንጌላውያን ግን በየዓመቱ ይፈራረቃሉ ድርሻቸውም ማቴዎስ ማርቆስ ዮሐንስ 365 ቀን ሲሆን የሉቃ 366 ቀኖች ይሆናሉ፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ ቀን በቤተክርስቲያን በእውቀት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሊቃውንት የበዓላትና የአጽዋማትን ቀኖች ለምእመናን የሚያሰሙበት ዕለት በመሆኑ     “ርዕሰ ዓውደ ዓመት ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ” ዮሐንስ የዓመቱ መጀመሪያ የመጥቅዕና የአበቅቴ አስገኝ ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡

መጥቅዕ የበዓላትና የአጽዋማት ማውጫ ሲሆን አበቅቴ ደግሞ ከሠርቀ መዓልትና ከሕፀፅ ጋር ተደምሮ የሌሊት ማውጫ ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ዓውደ ዓመት ዕለት ልብ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ ዐቢይ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከዓመት እስከ ዓመት የሠራነውን ሥራ ነው፡፡

ዘመን ፍጡራንን ሁሉ የሚያታግል የትግል መስክ ነው፡፡ እርስ በእርሳቸው የሚታገሉ ሰዎች ሁለቱም የድል ባለቤቶች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አንድ ጊዜ የማሸነፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመሸነፍ ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ግን አንድ ጊዜ ተሸነፍኩኝ ብሎ ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔርን ረዳትና አጋዥ አድርጎ ለመልካም ነገር መጣርና መታገል ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ዓለም ጠንክሮ ካልታገሉ ሥጋዊ ኑሮን አሸንፎ በሰላምና በደስታ ለመኖር አይቻልም፡፡ ሰው በሕይወተ ሥጋ እስከአለ ድረስ ጠንክሮ የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ እጅን አጣምሮ እግርን ኮርትሞ ቢመለከቱት ለውጥ አይገኝም፡፡

ዘመን የሥራን፤ የንቃትና የትጋትን፤ የፍቅርንና የሰላምን ተሳትፎ በብርቱ ይጠይቃል፡፡ ዘመን አልፎ ከሄደ በኋላ አይመለስም አስቀድሞ የተዘጋጀ ብቻ አብሮት ለመራመድ ይችላል፡፡

በዘመን የማይለወጥ ነገር የለም ዛሬ ያገኘው ነገ ያጣል ዛሬ ያጣው ነገ ያገኛል፡፡ ዛሬ በጽኑዕ የታመመው በሽተኛ ጥቂት ቀን ሰንብቶ ሊፈወስ ይችላል፡፡ ዛሬ ጤነኛ ነኝ የሚለው ከጊዜ በኋላ ደግሞ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ሊጨነቅ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር በደረሰ ጊዜ ዘመን አመጣብን ብሎ በዘመኑ ማመካኘት አይገባም፡፡ ዘመን የመስጠትና የመንሳት የማዳንና የማሳመም ሥልጣን የለውምና ሁሉም ያለፈጣሪ ሊፈጸም አይችልም፡፡ ዘመናትም ሆኑ ሌሎች ፍጥረታት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የደስታም ሆነ የችግር ምክንያቶች ለመሆን አይችሉም፡፡

ያለፈው ዓመት በጅቷቸው በዓውደ ዓመቱ የሚደሰቱ ሲኖሩ ዘመኑ ከፍቶባቸው እያዘኑ ያለፈውን ዘመን መልሰህ አታምጣብን የሚመጣውን ዘመን የደስታ አድርግልን በማለት እግዚአብሔር አምላክን የሚማጸኑ አሉ፡፡

አሳቡ መልካም ነው፡፡ ሁሉም ያለ እርሱ ፈቃድ አይሆንምና ለደስታም ሆነ ለኀዘን ለብልጽግናም ሆነ ለድህነት ምንጩ ዘመን እንደሆነ አድርገው የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አይታጡም፡፡

ዘመን ግን ታዛዥ እንጂ አዛዥ አይደለም፡፡ ዘመን ለሰው ልጆች የሥራ መሥሪያ እንዲሆን ከእግዚአብሔር የተሰጠ በመሆኑ በሰው ላይ መጥፎ ነገርን እንዲያመጣ የተፈጠረ አይደለምና፡፡

“ያለፈው ዘመን አልሆነኝም ይህ ዘመን ግን ይሆነኛል በይበልጥ ደግሞ ከርሞ የሚመጣው ክፍሌ ነው” እያሉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚደልሉ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ ይህ ሁሉ ከንቱ አስተሳሰብ ስለሆነ እግዚአብሔርን ረዳት አድርጎ ሳይጠራጠሩ ጠንክሮ መሥራት ከማንኛውም ችግር ሊያድን ይችላል፡፡

አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ሲተካ ባለፈው ዘመን የሠሩትን ሥራ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ የሰነፈ ቢኖር ባለመሥራቱ ተጸጽቶ ለወደፊቱ ጠንክሮ ለመሥራት ታጥቆ መነሣት አለበት፡፡ ክፉ ሥራ ሠርቶ ከእግዚአብሔር አንድነት የተለየ ቢኖርም ንስሓ ገብቶ ወደ ፈጣሪው ለመቅረብ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ኃጢአት የሠራችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” /1ኛ ጴጥ. 4÷3/ በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህ መሠረት ዘመን ሲለወጥ እኛም መለወጥ አለብን፡፡ ርዕሰ ዓውደ ዓመት ተብሎ የተሰየመውን የዓመት መጀመሪያ ስናከብር አዲሱን ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የበረከትና የደስታ ዘመን እንዲያደርግልን እግዚአብሔርን በመለመን ነው፡፡

በአዲሱ ዘመን ከእስካሁኑ የተሻለ ሥራ ሠርተን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡

                                               ወስብሐት ለእግዚአብሔር

     ከላእከ ወንገል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ ­