ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ እና ታላቁ ኢማም አል አዝሃር የተቀበሉት የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሠነድ ለኢትዮጵያም ይጠቅማል….. ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

ዛሬ አሜን ኢትዮጵያ የተባለ በኢትዮጵያውያን የተመሰረተ ስለሠላም ስለአንድነት አብዝቶ በሚሰራ ማህበር አማካኝነት በኢሲኤ (eca) አዳራሽ በተዘጋጀ ውይይት ላይ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና እንደ አዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ሰብሳነነታቸው ተገኝተው ስለሰው ልጆች ወንድማማችነት እና እህትማማችነት መልክት አስተላልፈዋል- ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።

ብፁዕነታቸው የሁለቱ ሀይማኖት አባቶች ስለሰው ልጆች ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ስለ ዓለም ሰለም እና አብሮነት ማሰብን አድንቀው የሁለቱ አባቶችን የስምምነት ሠነድም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀብሎ ያፀደቀው እንደመሆኑ ይሄ ለኛይቱ ኢትዮጵያም ይጠቅማል ብለዋል።

ዘር፣ ጎሣ፣ ሀይማኖት፣ ጾታ ሳይለይ የሰው ልጆች ሁሉ በዓለም ላይ ሲኖሩ በአብሮነት እህቴ ወንድሜ በሚል መንፈስ እንድንኖር በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በዚህ መድረክ ተገኝታ ድጋፏን ገልጻለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከገባችበት አሁናዊ ቀውስ መውጫ መንገዱ ስለሰላም እና አብሮነት ስለወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስ ቀድሞ ይኖርበት የነበረው አብሮነት ዛሬ አደጋ ላይ ስላለ ይሄን አብሮነት ለመመለስ አሜን ኢትዮጵያ ጠንክሮ መስራቱን በእሰየው አድንቀዋል።

በታሪክ ኢትዮጵያ በውጪ ወራሪ የልውረር አትወርም ምክንያት ብዙ ጦርነት ማድረጓን ጠቅሰው አሁን ላይ የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ በመሆናችን እንዲህ አይነት ዓለማቀፋዊ የሰላም እና አብሮነት ጥናትና ምክክር መፈጠሩ በጥሩ ጊዜ በመሆኑ የሚደገፍ ነው ብለዋል።

ሁለቱ የክርስትና እና የእስልምና አባቶች የተፈራረሙት ሠነድ ስለ ሀይማኖት ፣ስለቀኖና፣ ስለዶግማ ሳይሆን ስለሰው ሰላም እና አብሮነት በመሆኑ ሁሉም የሚቀበለው ትክክለኛ ሠነድ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አቋሟን ገልጻች ብለዋል።

እምነት የግል ነው ሀገር የጋራ ነው ከሚል ወረቃማ አባባል ሰላምም የጋራ ነው ወደሚል መምጣት አለብን ሲሉ ብፁዕነታቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

አሜን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የሰው ልጆች ወንድማማችነት ላይ ባተኮረ ጥናት እና ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች አባ ገዳዎችና ጥናት አቅራቢ ምሁራንም ተገኝተዋል።

በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
  4. ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese