ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ: ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ
በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ቀን ዓመታዊ ክብረ በዓል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ ዕለቱን በተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ፣ መንፈሳዊ ትምህርትና ወቅቱን በተመለከተ አባታዊ ምክር በብፁዓን አባቶችና በሊቃውንት ቀርቧል።
በሊቃውንት “ይቤላ ሰሎሞን ለማርያም ርግብየ ሠናይት…፤ በገዳሙ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንም (ጽርሕ ንጽህት ማርያም: ተፈስሒ ሀገረ እግዚአብሔር፡ ቃል ቅዱስ ይወጽእ እምኔኪ አእላፍ መላእክት ይትለአኩኪ” የሚል ዕለቱን በተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ በድምቀት ተዘምሯል።
ትምህርት ከመሰጠቱ በፊት በገዳሙ ም/ሊቀ መንበር ዓመታዊ ሪፖርት የተነበበ ሲሆን፡ በገዳሙ ዘርፈ ብዙ መሠረተ ልማቶች መከናወናቸው እና እየተከናወኑ መሆናቸውን ተገልጿል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ገዳሙ ከ30 በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ያፈራና የሊቃውንት መፍለቂያ መሆኑን ታውቋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለኃይማኖት ወልዱ ‘ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ’፤ ሕዝብሽ/ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ’ (መዝ 44:10) በሚል መነሻነት በዓሉን የሚገልጽ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በዓሉን በተመለከተ ታሪኩን ዘርዝረው በስፋት ያስተማሩ ሲሆን፣ በዓሉ በስዕለት የተገኘች ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕዝቧና ያባቷን ቤት ትታ ወደ ንጹህ ቤተ መቅደስ መግባቷ እያሰብን እኛም ኃጢአት፣ በደል፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ቂምና በቀል ረስተን/ትተን ወደ ቅድስና መግባት አለብን ብለዋል።
ቅዱስ ዳዊት በብሉይ ኪዳን “እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ፤ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ” (መዝ 65:13) እንዳለው እኛም ራሳችንን መሥዋዕት አድርገን ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንዳለብን አስተምረዋል።
አክለውም የእያቄምና የሐና ጸሎት ሰምቶ ችግራቸውን የፈታ አምላክ ዛሬም ችግራችን እንዲፈታልን ስለ ሀገራችን አጥብቀንና አብዝተን መጾምና መጸለይ አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም በበዓሉ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ፣ እርሱም ያበራላቹኋል በሚል መነሻነት አባታዊ ምክርና ቡራኬ በመስጠት መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተውታል።
በክብረ በዓሉ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማ እና ጌድኦ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በአመሪካ የኮሎራዶና አከባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፀዕ አቡነ ናትናኤል፣ በመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መ/አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለኃይማኖት ወልዱ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ኪዳነ ማርያም፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ሠናያት የቻለው፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንትና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
በመ/ር ኪደ ዜናዊ