ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን(ሥርዓቴን ጠብቁ)
በላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአ/አ/ሀ/ስ/የስብከተ ወንጌል ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ
“ሥርዓቴን ጠብቁ”
ዘሌዋ. 19፡19
ሥርዓት፡- ቃሉ ግዕዝ ነው፡፡ ሠርዐ፡ ሠራ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ሥርዓት ማለት ሕግ፣ ደንብ ማለት ነው፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማለት የቤተክርስቲያን ሕግ የቤተክርስቲያን ደንብ ማለት ነው፡፡ ከላይ በጽሑፉ መነሻ እንደተጠቀሰው ሥርዓት መጠበቅ እንዳለብን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር አዟል፡፡
በቤተክርስቲያናችን የሚፈጸሙ ብዙ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ሄደን ገና ከውጭው በር ላይ ስንደርስ ስመ ሥላሴን እየጠራን በትእምርተ መስቀል እያማተብን “ሰላም ለኪ አምሳለ ኢየሩሳሌም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” (የኢየሩሳሌም አምሳል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም ላንቺ ይሁን) እያልን ሦስት ጊዜ ለቤተክርስቲያን ሰላምታ እንሰጣለን፡፡
ለቤተክርስቲያን ሰላምታ መስጠት እንደሚገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለቤተክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ” የሐዋ. ሥራ 18፡22
ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ከገባን በኋላ ወደ ውስጥ እንገባል ስንገባም ወንዶች በወንዶች በር፣ ሴቶች በሴቶች በር ካህናትም በካህናት በር ይገባሉ፡፡ የሚሳለሙትም ሁሉም በየበራቸው ነው፡ ውስጥ ከገባን በኋላ ወንዶች በወንዶች መቆሚያ ሴቶች በሴቶች መቆሚያ ይቆማሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ሴቶች ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ራሳቸውን መከናነብ አለባቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡5
በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ የሚፈጸሙ ብዙ ሥርዓቶች አሉ
በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ከሚፈጸሙት ሥርዓቶች ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡
በቅዳሴ ጊዜ ለቅዳሴ ከተሰየሙት ልዑካን በስተቀር መውጣት፣ መግባት፣ መዘዋወር አይፈቀድም፡፡ የተቻለው ተሰጥዎውን መቀበል ያልተቻለው በጽሙና ሆኖ ጸሎተ ቅዳሴውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት” (ለእግዚአብሔር በፍርሃት ስገዱ) ይላል ሁላችንም በግምባራችን ተደፍተን እንሰግዳለን ቄሱ ፍትሐት ዘወልድ ይደግማሉ በመቀጠል ዲያቆኑ በእንተ ቅድሳት ይደግማል፡፡ ከዚያም ዲያቆኑ
“ተንሥኡ ለጸሎት” (ለጸሎት ተነሡ) ይላል ሰግደን የነበርነው እንነሳለን ይህ ምሳሌ አለው፡፡ ስገዱ ሲለን መስገዳችን በኃጢአት የመውደቃችን ምሳሌ ነው ተነሡ ሲለን መነሣታችን ደግሞ
በንስሐ የመነሣታችን ምሳሌ ነው፡፡ ስገዱ ሲባል ቁጭ የሚሉ ሰዎች አሉ ይህ ከሥርዓት ውጭ ነው ስገዱ እንጂ ቁጭ በሉ አልተባለም፡፡ ሆኖም፡-
1.እድሜያቸው የገፉ ሽማግሌዎች፤
2.ሕመምተኞች ከእነዚህ በስተቀር ሁሉም መስገድ አለበት፡፡
እንዲሁም ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ “የተቀመጣችሁ ተነሡ” ይላል ቁጭ ያለ ይቁም ማለት አይደለም፡፡ በፊቱኑ መች ቁጭ በሉ ተባለና ቆመን እንድናስቀድስ ነው ሥርዓት የተሠራው በዚህ መሠረት “የተቀመጣችሁ ተነሡ” ማለት ምሥጢሩ በኃጢአት የወደቃችሁ በንስሐ ተነሡ ማለት ነው፡፡
እንዲሁም በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ይላል ፊትን ዞር አድርጎ ወደ ምሥራቅ መመልከት አይደለም፡፡ ይህ እጅግ በጣም ሰፊ ምስጢር ያለው ሲሆን ጥቂቶቹን እንገልጻለን፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ምሉዕ ሲሆን ይህን ዓለም ለማሳለፍና ለፍርድ የሚመጣው በምሥራቅ በኩል ነው ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ሲል ምስጢሩ ምጽአተ ክርስቶስን (የክርስቶስን መምጣት) አስቡ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በፀሐይ መውጫ በምሥራቅ የተመሰለችው እመቤታችንን አስቡ ማለት ነው፡፡ ሌላው በምሥራቅ የምትገኝ ገነትን አስቡ ማለት ሲሆን ይህም ገነት ለመግባት የሚያበቃ መልካም ሥራ ሥሩ ማለት ነው፡፡
አንዳንዶቹ ምዕመናንና ምዕመናት “አሜን” ሲባል ቅዳሴው ተፈጸመ ብለው ወደቤታቸው ይሄዳሉ አለማወቅ ነው የጸሎተ ቅዳሴው የመጨረሻ የማሰናበቻ ቃል “ዕትው በሰላም” (በሰላም ግቡ) ነው፡፡
ሌላው በዚሁ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚካተተው ትምህርት በቅዳሴ ጊዜ የግል ጸሎት መጸለይ ክልክል ነው፡፡ ምክንያቱም በቅዳሴ ጊዜ የግል ጸሎት መጸለይ ማለት ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ከሚሆንበት ከቅዳሴው ጸሎት ይልቅ የእኔ የግል ጸሎት ይበልጣል ማለት ነው፡፡ በፀሐይ ብርሃን ላይ ሻማ እንደማብራት ነው የሚቆጠረው ስለዚህ ከቅዳሴው በፊት ቀደም ብለን መጥተን የግል ጸሎታችንን መጨረስ አለብን፡፡
እንግዲህ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው ስላስጠበቁ ሰማያዊ በረከት ተጎናጽፈዋል፡፡ ሌሎችም ቅዱሳን (ደጋግ ሰዎች) የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው ተጠቅመዋል፡፡ በአንጻሩ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሳይጠብቁ ቀርተው የተጎዱ አሉ፡፡ ለምሳሌ ንጉሡ ዖዝያን ባልተሰጠው ሥልጣን ከሥርዓት ውጭ በመሆን ቤተ መቅደስ ገብቼ አጥናለሁ ብሎ ገባ፤ ሰማንያ ካህናት ተሰብስበው ተው ይህ ላንተ አልተፈቀደም በድለሃልና ከቤተ መቅደስ ውጣ ብለው መከሩት እርሱ ግን ምክራቸውን አልተቀበለም፡፡ ቤተ መቅደስ ገብቶ ጽንሐውን ይዞ አጠነ ወዲያው በግምባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት እስኪሞት ድረስ ለምጹ ከሰውነቱ ላይ አልጠፋም፤ ካህናቱም ፈጥነው ከመቅደስ አስወጡት፡፡ 2ኛ ዜና 26፡ 16-23
ሌሎችም ሥርዓት ሳይጠብቁ ቀርተው የተጎዱ አሉ፡፡ እኛም እንደ እነርሱ እንዳንጎዳ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት እንጠብቅ፡፡ ሥርዓት የማይጠብቁ ወገኖቻችንንም በትሕትና ቃል እንምከራቸው፣ እንገሥጻቸው፡፡ “ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው” 1ኛ ተሰ. 5፡14
“ሁሉ በአገባብ እና በሥርዓት ይሁን” 1ኛ ቆሮ. 14፡40
በዚህ ቅዱስ ቃል መሠረት በአጠቃላይ የክርስቲያን አኗኗር በሥርዓት መሆን ይገባዋል፡፡
የቤተክርስቲያናችንን ሥርዓት ጠብቀን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ አማላካችን ልዑል እግዚአብሔር ወሠን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡
{flike}{plusone}