መምህር ጎይቶኦም ያይኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ!!
መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የካቲት 13 ቀን 2009 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነትን በተመለከተ የተለየ አደረጃጀት የለውም፤ የምንሠራው ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠችው አሠራር ነው፤ በቃለ ዓዋዲው መሠረት ሀገረ ስብከቱ የተለያዩ ክፍሎች አሉት፤ የሁሉም ክፍሎች በተሣካ አደረጃጅ ተደራጅተዋል፡፡
በየክፍሉ ንዑሳን ክፍሎች አሉ፤ አዲስ አበባ ከተማ በክፍላተ ከተማ አወቃቀር አስር ክፍላተ ከተማ ነው ያለው፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሥር ግን የተዋቀሩት የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሰባት ክፍላተ ከተማ ናቸው፤ የአንዱ ክፍለ ከተማ መዋቅር ሦስት ክፍለ ከተሞች ጠቅልሎ የያዘ ነው፤
ለምሳሌ አዲስ ክፍለ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ልደታ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር እንደ አንድ ክፍለ ከተማ ይቆጠራል፤ በዚህ መሠረት በሀገረ ስብከቱ ሥር ሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት አሉን ማለት ነው፡፡
በሌላው ሀገረ ስብከት እንደሚታወቀው ከሀገረ ስብከቱ ቀጥሎ ያለው ወረዳ ቤተ ክህነት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ ግን ወረዳ ቤተ ክህነት የሚል ክፍል የለም፡፡ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተብሎ የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ነው የሚባለው፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ያሉት ገዳማትና አድባራት ብዛት እስከ 2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ድረስ 180 ነበር፤ በዚህ ዓመት የገዳማትና አድባራት ብዛት በጠቅላላ 198 ደርሷል፡፡
በዚህ በዓቢይ ጾም ውስጥ የሚካሄደውን መንፈሳዊ አገልግሎት በተመለከተ እንደማንኛውም ጊዜ ተመሳሳይ ቢሆንም እንኳን በክርስቶስ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንደምትሰብክ የታወቀ ሲሆን በቀኖናዋ መሠረት እያገለገለች ትገኛለች፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ በተሻለ መጠን ለምዕመናን ብቁ አገልግሎት በማጠናከር ከሌላው ጊዜ በጾሙ ወራት ምዕመናን ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ አምልኮታቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ፣ በተለይ በስብከተ ወንጌል ደረጃ ለየት ያለ በገዳማቱና በአድባራቱ የአንድነት መርሐ ግብር አለ፡፡
ስለዚህ አንድነት ጉባኤው ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴና የተጠናከረ ክትትል እያደረግን ነው ያለ ነው፡፡ በሀገረ ስብከት ደረጃ ብቻ ሳይሆን እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ከምን ጊዜም በበለጠ ክትትልና ቁጥጥር ያለው የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር፣ በጸሎተ ምሕላም፣ በስብከተ ወንጌልም፣ በሥርዓቱና በቀኖናው መሠረት እንዲካሄድ እየተደረገ ነው፡፡ አዳዲስ በተተከሉ አብያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሥርዓተ አምልኮው ወይም የሱባኤው መርሐ ግብር በተጠናከረ መልኩ እየሄደ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፤ በሁሉም ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል መምህራን ተመድበዋል፡፡
እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት የተለየ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ለሰባት ቀናት ያህል ጸሎተ ምሕላና ጸሎተ ፍትሓት እንዲደረግ በተላለፈው መመሪያ መሠረት በገዳማቱና በአድባራቱ ሥርዓቱ እንዲደርስ ተደርጓል፤ በአደጋው የሞቱትን ወገኖቻችንን እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በገነት እንዲአኖርልን እና እረፍተ ነፍስ እዲሰጥልን በሁሉም ገዳማትና አድባራት ምህላው በአግባቡ እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡
በአደጋው ወደ ተጎዱት ወገኖቻችን በአካል በመሄድ ለማጽናናት ችለናል፤ አሁንም ቢሆን ገዳማቱና አድባራቱ አስተዋፅኦ እንዲአደርጉ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው የሚገኘው፤ እንደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለተጎዱት ወገኖች በአዲስ አበባ መስተዳደር በተቋቋመው ኮሚቴ በኩል አንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፤ ይህ አሠራር በሁሉም አጥቢያዎች ይቀጥላል፤ እንኳንስ ወገኖቻችንን ቀርቶ ማንኛውንም ሰብአዊ ፍጡር መርዳት አለብን፡፡
የተለያዩ ኮሚቴዎችም ተዋቅረዋል፤ በዚሁ መሠረት በየጊዜው ክትትል እያደረግን የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን፤ ወቅቱ የሱባኤና የጾም ጊዜ በመሆኑ ገዳማትና አድባራት በሥራቸው ያሉ አገልጋዮች፣ እንደዚሁም በየአጥቢያው ያሉ ምዕመናን ሱባኤውን ምክንያት በማድረግ በተለየ መልኩ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ስለሚገባቸው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም ጥረት ማድረግ አለብን፤ በጾም ጊዜ ሲባልም ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ተለይቶ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡
ነገር ግን ሱባኤ ሲሆን በተለየ መልኩ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ጊዜና የተሻለ ሁኔታ በመፍጠር ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን ለማለት ነው፡፡
ስለዚህ ምዕመናን በተረጋጋና በሰላም ሥርዓተ አምልኮታቸውን እንዲፈጽሙ ስብከተ ወንጌል በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ቁጥጥርና ትጋት ያስፈልጋል፡፡ በልማቱም ዘርፍ ቢሆን የተሻለ ልማት እንዲኖር የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ምዕመናን የሚሰጡትን ገንዘብ በአግባቡ በመሰብሰብ ቤተ ክርስቲያን በአግባቡ እንድትለማ፣ ወቅቱ የሚጠብቀውን ሥራ ለመሥራት እስከ አሁን ድረስ አባቶቻችን ይህችን ቤተ ክርስቲያን በአግባቡ ጠብቀው አቆይተውልናል፤ እኛም ደግሞ እግዚአብሔር ፈቅዶ እዚህ ጊዜ ደርሰናል፡፡
ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆን ወቅቱ የሚጠይቀው ሥራ ለመሥራት የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለብን፡፡
መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ