መምህር ይቅርባይ እንዳለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ምክትል ሓላፊ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት ሰባኬ ወንጌል መምህር ይቅርባይ እንዳለ በቁጥር 113-28/2010 በቀን 20/10/2010 ዓ.ም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጻፈ ደብዳቤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት በሆነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዋና ሥራ አስኪያጅነት ተመድበዋል፡፡
ለዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ይቅር ባይ እንዳለ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተጻፈላቸው የሹመት ደብዳቤ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሲሆን መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ካህናትንና ማኅበረ ምዕመናንን፣ በፍቅርና በአንድነት በመምራት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከርና በማደራጀት፣ የሀገረ ስብከቱን የልማት ሥራ በማጠናከርና የቃለ ዓዋዲውን መመሪያ በማስፈጸም የተሰጣቸውን ከባድ ሓላፊነት በትጋትና በብቃት እንዲወጡ ያብራራል፡፡
መምህር ይቅርባይ እንዳለ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን የሥራ መስኮች በኃላፊነት እየተመደቡ ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በሠሩባቸው የሥራ ቦታዎች ሁሉ መልካም ስም እንዳላቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
የትምህርት ዝግጅታቸውን በተመለከተ በነገረ መለኮት በድግሪና በማስተርስ መርሐ ግብር የተመረቁ ሲሆን በዘመናዊ ዕውቀታቸውም የድግሪ መርሐ ግብር ምሩቅ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በስብከተ ወንጌል አገልግሎትም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ እየተዘዋወሩ የሚሰብኩና የሚያስተምሩ፣ ጥዑም ልሳን ያላቸውና አንደበተርቱዕም ናቸው፡፡ በአፋን ኦሮሞ የጋዜጠኝነት ሥራ ሲሠሩ እንደነበረ መረጃዎቻቸው ያስረዳሉ፡፡
ለመምህር ይቅርባይ እንዳለ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው የዝግጅት ክፍላችን ይመኝላቸዋል፡፡
በሌላ ዜና ያለአግባብ ከሥራ ተፈናቅለናል በማለት የሀገረ ስብከት፣ የክፍለ ከተማ ቤተክህነት፣ የገዳማትና አድባራት የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት ክስ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ትእዛዝና መመሪያ አጣሪ ልዑክ ተመድቦ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ይገኛል፡፡