“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ”
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ ኣህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዲስ ዋና ጸሓፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና የሓዲያ ስልጤ ኣህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡራን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣
ክቡራን ኣምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
የተከበራችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ኣገልጋዮችና ሰራተኞች፣ምእመናንና ምእመናት፣
በኣጠቃላይ በዚህ በዓለ ሢመተ ክህነት የተገኛችሁ በሙሉ፤
ጸጋውን እያበዛልን ከዚህ ዕለት ያደረሰን እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለዓሥራ ሦስተኛው በዓለ ሢመተ ክህነታችን ኣደረሰን አደረሳችሁ!
“ወቦቱ ረከብነ ጸጋ ወተሠየምነ ሓዋርያተ ከመ ናስምዖሙ ለኣሕዛብ ወይእመኑ በስሙ፤በስሙ ያምኑ ዘንድ ቃለ ወንጌልን ለኣሕዛብ እንድናሰማ የተሾምንበት ሓዋርያነት ከሱ የተገኘ ጸጋ ነው›› (ሮሜ.፩÷፭)፤
ይህ ጥቅስ ሓዋርያት ተብለን የተሾምንበትን ፍሬ ነገር ይገልጻል፤የተሾምንበትም ዋና ምንክያት ስሙን ለኣሕዛብ ልናስተምር እንደሆነ ያስረዳል፤የማስተማር ውጤት ደግሞ ሰዎች በስሙ ኣምነው እንዲድኑ ማድረግ እንደሆነ ያመለክታል፤የካህናተ እግዚአብሔር ዓቢይ ተልእኮም ይህ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤
በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የኣገልግሎት ዘርፎች ቢኖሩም፣ መዳረሻቸው ቃለ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማብሰር ነው፤ የክህነት ኣገልግሎታችን በተመደበለት ቦታ ላይ ያለ መሆኑን መመዘን ያለበትም በዚህ መለኪያ ነው፤ ዛሬ የምናከብረው በዓለ ሢመትም ይህንን ተልእኮ ማእከል ያደረገ ነው፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡራን እንግዶች!
የዘመናችን ሓዋርያት የሆን ሁላችን ቃለ ወንጌልን በትክክል ለሕዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ እሱን በኣግባቡ ማስተላለፍ ከቻልን፣ማኅበረ ሰባችንን ከልዩ ልዩ ተፈናዎች መታደግ እንችላለን፤ ከዚህም ጋር በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን በየጊዜው ብቅ ጥልቅ የሚሉ ፈተናዎችን ለመከላከል በንጹህ ልቡና በትሑት ሰብእና ሆነን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ፤እንደዚሁም ከግል ፍላጎትና ኣስተሳሰብ በጸዳ ሁናቴ ቃለ ወንጌል በማስተማር ኅብረተሰቡን በሃይማኖትና በሥነ-ምግባር እንጠብቅ፤ ይህንን በብቃት ለመወጣትም ከሁሉ በፊት ራሳችንን ክደን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች የተሟላ ደኅንነት በጽናት እንቁም፤
በመጨረሻም፡-
ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን ከፍተኛ ኃላፊነት ተገንዝበን የእግዚአብሔር ሠራዊት የሆኑትን ምእመናንንና እግዚአብሔርን በቅንነት እናገልግል በማለት ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
በድጋሚ እንኳን ለዓሥራ ሦተኛው በዓለ ሢመተ ክህነት በሰላም አደረሳችሁ!
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፰
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
