መልአከ ገነት ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
የቀደሞው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት መልአከ ገነት ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመድበዋል፡፡
መልአከ ገነት አባ አፈወርቅ በመንፈሳዊና በዘመናዊ የትምህርት ሙያና እስከአሁን ድረስ የአገለገሉባቸውን የሥራ መስኮች አስመልክተው ለዝግጅት ክፍላችን በገለጹልን መሠረት በቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሙያዎች ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከሚገኙት መምህራን የውዳሴ ማርያም ዜማ፣ የዳዊት ንባብ፣ አስራአራቱን ቅዳሴያት አጥንተዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ መንፈሰዊ ኮሌጅ በነገረ መለኮት ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት የሐዲሳት ትርጓሜ ተማሪ ናቸው፡፡
በተለያዩ የሥራ መስኮች እየተመደቡ ያገለገሉባቸውን የሥራ ቦታዎችም እንደሚከተለው ገልፀውልናል፡፡ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲፕሎማ መርሐ ግብር እንደተመረቁ በምዕራብ ሸዋ (አምቦ) ሀገረ ስብከት በሊቀ ካህናትነት የኃላፊነት ሥራ ከ3 ባላነሱ የወረዳ ቤተ ክህነት በሥራ አስኪያጅነት ሥራ፣ የምዕራብ ሸዋ (አምቦ) ሀገረ ስብከተ በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ሥራ፣ በቡራዩ ቅዱስ ሚካኤል በአስተዳዳሪነት ሥራ፣ በወሮጉድሩ ሀገረ ስብከት በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣/ለአራት ዓመታት/ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ (ወሊሶ) ሀገረ ስብከት በዋና ሥራ አስኪያጅነት /ሁለት ዓመታት/፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት አገልግሎት ሥራ፣ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በሥራ አስኪያጅነት ለአንድ ዓመት ያህል ሠርተዋል፡፡
በክፍለ ከተማው የኃላፊነት ሥራ ቆይታቸው በአድባራትና ገዳማት ይታይ የነበረውን አለመግባባት ከየአድባራቱና ገዳማቱ ድረስ በመጓዝ በውይይት እንዲፈታ በማድረግ በክፍለ ከተማው ሰላምንና መረጋጋትን አስፍነዋል፡፡ በማህበራት ዙሪያ የነበረውን ሽኩቻና መገፋፋት እንዲወገድ አድርገዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ባለፈው የበጀት ዓመት ያስመዘገበው የፐርሰንት ክፍያ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ሲሆን መልአከ ገነት ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በሠሩባቸው ውስን ወራቶች አስራ አምስት ሚሊዮን ብር የፐርሰንት ገቢ በማስመዝገብ የስድስት ሚሊዮን የፐርሰንት ገቢ ብልጫ አስመዝገበዋል፡፡ በክፍለ ከተማው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እንዲስፋፋና የአንድነቱ ጉባኤ አንዲጠናከር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ሰበካ ጉባኤን በማጠናከርም ብዙ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በአድባራትና ገዳማት እየታነፁ የሚገኙ ሕንጻ ገዳማት ወአድባራት ለውጤት እንዲበቁ በማስተማረና በመቀስቀስ ከፍተኛ ውጤት አሳይተዋል፡፡
ስለሆነም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የመልአከ ገነት ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስን የሥራ ተነሳሽነት፣ ግብረ ገብነት፣ ሁለንተናዊ ሙያ፣ የአመራር ብቃት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሹመት ደብዳቤ ሰጥተዋቸዋል፡፡