መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ የሰጡትን አባታዊ አገልግሎት አስመልክቶ የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል እንዲሁም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ በተገኙበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለተመደቡት ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንገሤ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ የሰጡትን መልካም አባታዊ አገልግሎት አስመልክቶ የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ።
መርሐ ግብሩም በብፁዕነታቸው ጸሎት እና ቡራኬ ተከፍቶ መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ቆሞስ አባ አትናቴዎስ ወልደ ጎርጎርዮስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል እና የሥራ አመራር መንፈሣዊ ኮሌጅ ርእሰ መምህር እና በመ/ር ዳዊት ቅኔ ቀርቦ በአዘጋጅ ኮሚቴዎች በኩል የሽልማትና የሥጦታ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
መርሐ ግብሩ የተካሄደው በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ሲሆን መጋቤ ሐዲስ ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ተስፋ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል ።
በመቀጠል የአዘጋጅ ኮሚቴው አስተባባሪ ክቡር መልአከ ብርሃናት ቆሞስ አባ ማርቆስ ብርሃኑ የአዳማ ናዝሬት ደ/ፀ/ቅ/ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ ከሐሳብ ጀምሮ በተግባር እንዲህ የአማረና የተዋበ ደማቅ መርሓ ግብር እንዲዘጋጅ የብፁዕነታቸው አባታዊ መመሪያ መሆኑን ጠቅሰው መልካም ሽኝት ለተደረገላቸውና አቀባበል ለተደረገላቸው ምኞታቸውን የሥራ ዘመንን ተመኝተዋል ።
በመቀጠልም ክቡር መልአከ ምሕረት ቆምስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዋና ሥራ አስኪያጁ የተደረገላቸውን የምስጋና መርሐግብር አስመልክተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን እግዚአብሔር ፈቅዶና ወዶ ከብፁዕነታቸው ጋር በልጅነት መንፈስ ከዝዋይ ገዳም ጀምሮ መመሪያ እየተቀበልኩ ሳገለግል ቆይቻለሁ ሀገረ ስብከቱንም በዋና ሥራ አስኪያጅነት በምመራበት ወቅት ከሀገረ ስብከቱ የየክፍሉ ሠራተኞች የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች አጠቃላይ አገልጋዮች በሙሉ በፍቅር በአንድነትና በመከባበር ስናገለግል ቆይተናል ይህ ደግሞ የብፁዕነታቸው አቡነ ጎርጎርዮስ ጸሎት ድጋፍ ሆኖን ነው። ዛሬ ደግሞ ታላቅ የሆነውን ፍቅራችሁን አሳይታችሁኛል። ከልብ አመሰግናለሁ የበለጠ ራሴን ሰጥቼ ቤተክርስቲያኔን ማገለገል እንድችል በጸሎታችሁ አስቡኝ በማለት ለተተኩ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
በመጨረሻም አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው ይኽ መርሐግብር የፍቅር የአንድነትና የመልካም ምኞት መርሐግብር ነው። መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ቤተክርስቲያንን በቅንነት ያገለገሉ ከእኔ እግር ስር ሆነው የማዝዛቸውን ሁሉ እሺ እያሉ የሚተጉ ትጉኅ አገልጋይ ናቸው። በምሥራቅ ሸዋ በነበራቸው አገልግሎት በከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም ከሁሉም ጋር በፍቅር መመሪያን ሳይጥሱ ያገለገሉ አባቶችን የሚያከብሩ እውነተኛ ልጃችን ነው። ዛሬ ሀገረ ስብከቱ ፍቅሩን ለመግለጽና በሄዱበት ሁሉ ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ በርቱ ለማለትና አደራ ለማለት ጭምር ነው የተሰበሰብነው።
በቅንነት ያገለገለ ለቤተክርስቲያን የታመነ ከፍ ከፍ ይላልና ቀሪ ያገልግሎት ዘመናቸው የተባረከ እንዲሁ አምላከ አበው ይከተላቸው ብለዋል።
በመርሓ ግብሩ ላይም ብፁዕነታቸውን ጨምሮ ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክብር መልአከ ሣህል ቀሲስ ነጋሽ ሀብተ ወልድ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ጌቱ ሞቲ የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ የአዲስ አበባና የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ክፍል ኃላፊዎች የወረዳው ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጆች የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች ሰባክያነ ወንጌል ሊቃውንት ቤተክርስቲያን አባ ገዳዎችና አደ ስንቄዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ ሰኔ 9/2017 ዓ/ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደተመደቡ የሚታወስ ነው።