መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ መስቀል አደባባይን አሰመልከተው በተናገሩት ቃል ሀገረ ስብከቱ መግለጫ እንደሚሰጥ ገለጸ
ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የአስተዳደር ጉባኤ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የመስቀል አደባባይ ጉዳይን አስመልክቶ “በቤተክርስቲያን ስም ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለው በሰጡት ንግግር ዙሪያ ተወያየ።
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ በጉባኤ ፊት ቀርበው ጥያቄም ተጠይቀዋል፡፡
ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል፦ በቤተክርስቲያኒቱ ስም ይቅርታ መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ቤተ ክርስቲያን አጥፍታ ነው ወይ? የሚሉት ይገኙበታል።
በጉዳዩም እጅግ በርካታ ምእመናንና የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማዘናቸውንና በርካታ ማኅበራትም ይህንን ጉዳይ ምክንያት አድርገው መግለጫ ማውጣታቸውን ለመልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ ተነግሯቸዋል፡፡
መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲመልሱ “እኔ ይቅርታ የጠየኩት ቤተ ክርስቲያን አጠፋች ብዬ አይደለም” ብለዋል፡፡
በዕለቱ መስቀል አደባባይ ስለነበርኩ ለአፍጥር የመጡትን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከፖሊስ ጋር በነበረው ግብግብና ግጭት ምንም የማያውቁ ህፃናትና ብዙ ሰዎች ሲያለቅሱ በመመልከት ነው እንደ አባት ይቅርታ የጠየኩት በማለት መልሰዋል፡፡
ይህንን ማለቴ ስህተት ከሆነ “ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት በተነሣው ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መ/ር አካለወልድ ተሰማ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ ይቅርታ የጠየቁበት መንገድ ስህተት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይቅርታ ተብሎ በመልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የተባለው ንግግር እንደ ተቋም ተነጋግሮ መግለጫ መስጠት ሲገባው በዚህ መልኩ ይቅርታ መባሉ ትክክል አይደለም ከአሁን በኋላ አይደገምም ብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ለወደፊት መግለጫም ይሁን ሌላ ጉዳይ እንዲሰጥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት በኩል እንዲሰጥ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የአስተዳደር ጉባኤ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የመስቀል አደባባይ ጉዳይን አስመልክተው በተናገሩት ንግግር ዙሪያ ሀገረ ስብከቱ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር አያይዞ ባሉት የቤተክርስቲያኒቱ ሚዲያዎች በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና በሌሎች የሥራ ኃላፊዎች መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጿል።
የዜናው ምንጭ፦ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ነው፡፡