መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ወአቡነ አዳም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩት መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ በቁጥር 3136/2012 በቀን 20/06/2012 ዓ.ም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጻፈ ደብዳቤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት በሆነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዋና ሥራ አስኪያጅነት ተመድበዋል፡፡
ለዋና ሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተጻፈላቸው የሹመት ደብዳቤ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሲሆን መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ካህናትንና ማኅበረ ምዕመናንን በፍቅርና በአንድነት በመምራት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከርና በማደራጀት፣ የሀገረ ስብከቱን የልማት ሥራ በማጠናከርና የቃለ ዓዋዲውን መመሪያ በማስፈጸም የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት በትጋትና በብቃት እንዲወጡ ያብራራል፡፡
መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ መስኮች በኃላፊነት እየተመደቡ ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በሠሩባቸው የሥራ ቦታዎች ሁሉ መልካም ስም እንዳላቸው ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
አገልግሎት ከሰጡባቸው ገዳማትና አድባራት በጥቂቱ፡-
- በቃሉ አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም ፣
- በእንጦጦ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ፣
- በአዲስ ዓምባ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ፣
- በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ፣
- በአየር ጤና ደብረ ዓባይ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ፣
- በአያት ጌቴሰማኔ ኪዳነ ምሕረት እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፣
- በደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ካቴድራል፣
- በምሥራቀ ፀሐይ ቅድስት አርሴማ እና ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ አዳም ቤተ ክርስቲያን በመሥራት የመሪነት ልምድን አካብተዋል፡፡
የትምህርት ዝግጅታቸውን በተመለከተ ከንባብ እስከ ጸዋትወ ዜማ ባደጉበት በደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ከሊቀ ጠበብት ጥላሁን ሠርፄ ተምረዋል፤ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ቅዳሴን በመምህርነት ደረጃ አጠናቀው ተመርቀዋል፤ በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ቅኔን ተምረዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ዲፕሎማቸውን ተቀብለዋል፡፡ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ፥ በአስተዳደር፣ በመሠረታዊ ኮምፒዩተር እና በቋንቋ ልዩ ልዩ ተዛማጅ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ተጨባጭ ክህሎት አጎልብተዋል፡፡ባላቸው ክህሎትና የዳበረ የሥራ ልምድ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መልካምና ውጤታማ ሥራ እንደሚሠሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ