“ልጆቻችሁን ወደ ቤተ ክርስቲያን አምጧቸው” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዓመታዊ ክብረ በዓልና የጻድቁ የአቡነ ዜና ማርቆስ የዕረፍት በዓል በጉራጌ ሀገረ ስብከት ስር በሚገኘው በምሁር ኢየሱስ ገዳም በጋራ ተከብሮ ዋለ።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበዓሉ ላይ ለተገኙት ምእመናን ትምህርት አስተላልፈዋል።
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሶስት ዓመት ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ እንደወሰዷት አውስተዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ መቅደስ ከተሰጠችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለዓለሙ ቤዛና መድኃኒት መሆኑን አያይዘው አብራርተዋል።
አክለውም ምእመናን ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና በመማር ልጆቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲያመጡ አጽንኦት ሰጥተው መልእክት አስተላልፈዋል።
ልጆች የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰሙ፣ቃሉን እየተማሩና እያነበቡ በቤተ ክርስቲያን ሲያድጉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆናሉ ብለዋል።
የጻድቁን የአቡነ ዜና ማርቆስን የወንጌል አገልግሎትና መንፈሳዊ ሕይወትም ብፁዕነታቸው አብራርተው አስተምረዋል።
የገዳሙ አበምኔት መ/ር ዘኢየሱስ ለብፁዕነታቸው “የእንኳን በሰላም መጡ” መልእክት አስተላልፈዋል።
ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምሁር ወረዳ ወንጌልን ለዓመታት ማስተማራቸውን አበምኔቱ አውስተዋል።
ከዚህም የተነሣ ብዙ ሕዝብ ወደ ቤተክርስቲያን እንደመለሱ ጠቅሰዋል።
በተያያዘም በምሁር ወረዳ በርካታ አብያተክርስቲያናት ተሠርተው ለአገልግሎት እንዲበቁ ያደረጉ ጻድቅ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የገዳሙ የአዲስ ኪዳን መምህር የሆኑት መ/ር ሀይለኢየሱስም ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን ሰጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ