“ልትድን ትወዳለህን?”
በመምህር ሣህሉ አድማሱ
በዐቢይ ጾም ከሚታሰቡት ሳምንታዊ ታሪኮች መካከል በአራተኛው ዕሑድ /ሰንበት/ የሚታሰበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ መጻጉዕ ይባላል፡፡
በዚህ ዕለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሌሊቱ አገልግሎት በዜማ የሚያሰሙት መዝሙር “አምላኩሰ ለአዳም” የሚለውን ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡
በጧቱ ሥርዓተ ቅዳሴ አገልግሎት ወቅት ደግሞ በዲያቆናቱና በቀሳውስቱ፣ በንባብና በዜማ የሚቀርቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክቶች ወንጌልና የዳዊት መዝሙር ሲሆኑ እነዚህም (ገላ5÷1) (ያዕ 5÷14) (የሐዋ 3÷1) (መዝ 40÷3) (ዮሐ5÷1-20) ናቸው፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊና አምላካውያት ቃላት መካከል በዳዊት መዝሙርና በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሱት እንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡ “ጸኒሐ ጸናሕክዎ ለእግዚአብሔር÷ ሰምአኒ ወተመይጠኒ፡፡ ወአውጽአኒ እምአዝቅተ ህርትምና ወእምፅቡር አምአም÷ ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት÷ እርሱም ዘንበል አለልኝ፣ ጩኸቴንም ሰማኝ፡፡ ከጥፋት ጉድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፡፡ ይህ ቃል ደራሲው ቅዱስ ዳዊት አስጨናቂ መከራ በከበበው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት ሲሆን የሐዘኑ መንስኤ ግን ምን እንደሆነ በውል አልጠቀሰውም፡፡
በደራሲው ላይ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት መሆኑን በቁጥር 12 ላይ ገልጾታል፡፡ ሥቃዩ የተባባሰበትም ጠላቶቹ በርሱ ሥቃይ በመደሰታቸው ምክንያት ነው፡፡
ደራሲው ጸሎቱን የሚጀምረው እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም ስላደረገለት ምሕረት ምስጋና በማቅረብና ለእግዚአብሔር ያሳየውን ታማኝነት በመግለፅ ነው፡፡ መዝሙረኛው እግዚአብሔር ረዳቱ እንዲሆን ልመናውን ያቀርባል፡፡
መዝሙረኛው ዳዊት በገጠመው ታላቅ መከራ ጊዜ እግዚአብሔር ባሳየው ቸርነት ለእግዚአብሔር ምስጋና እንዲያቀርብና ሌሎቹንም ወደ እምነት እንዲመራ አነቃቅቶታል፡፡
ከዚህ በላይ የተብራራው በዳዊት መዝሙር የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር ሲሆን በዮሐንስ ወንጌል 5÷1-20 ያለው ደግሞ እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
“ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ÷ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡
በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (ቤተዛታ) የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡ በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች፣ አንካሶችም፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር፡፡ በዚያም ከሠላሳ ሳምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ÷ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እነደ ነበረ አውቆ ልትድን ትወዳለህን? አለው፡፡ ድውዩም፡፡ ጌታ ሆይ÷ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚኖረኝ ሰው የለኝም፣ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት፡፡
ኢየሱስ ተነሣና አልጋሀን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፡፡ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡ ያም ቀን ሰንበት ነበረ፡፡ ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት፡፡ እርሱ ግን ያደነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው፡፡ እነርሱም አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማነ ነው? ብለው ጠየቁት፡፡
ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው፡፡ ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ለአይሁድ ነገረ፡፡
ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፤ ኢየሱስ ግን አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ አሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው፡፡ እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም÷ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስከተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡
ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፣ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና፡፡”
ወንጌላዊ ዮሐንስ የሕመምተኛውን የበሽታ አይነት አልገልጸውም፡፡ ሕመምተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ከበሽታው እንዲፈውሰው ባይጠይቀውም የሰውዬው የመዳን ተስፋ ስለተሟጠጠ ልትድን ትወዳለህን የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ ነበር፡፡ በሽተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ ሊሆን ይችላል ብሎ ስላልገመተ ልቡን የጣለው ያድናል ተብሎ በሚታመነው በቤተ ሳይዳ (በቤተዛታ) የመጠመቂያ ውሃ ነበር፡፡
በሽተኛው የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት አያውቅም ነበርና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ የሚአድነው እምነት ያለውን ሰው ነው፤ ሆኖም ግን ለምሕረቱ ልክ የሌለው እና እጅግ አዛኝ መሲሕ በመሆኑ በሽተኛው ማመን ሳይጠበቅበት ከበሽታው ፈወሰው፡፡ የመጻዕ ልብ ያረፈው የእግዚአብሔር መልአክ አልፎ አልፎ በሚያናውጠውና በርካታ በሽተኞች በተራ በሚፈወሱበት የቤተ ሳይዳ (ቤተዛታ) ውሃ ላይ ብቻ እንጂ የማዳን ኃይል ባለው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አልነበረም፡፡
ይህ የማዳን ኃይል የተፈጸመው በሰንበት ቀን ማለትም ቅዳሜ ዕለት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ መሠረት አንድ ሰው በሰንበት ዕለት ምንም አይነት ሥራ መሥራት የለበትም፡፡ (ዘፀ20÷8) በሕጉ መሠረት በሰንበት ቀን አልጋም ሆነ ምንጣፍ መሸከም አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም አልጋን ተሸክሞ መሄድ እንደሥራ ይቆጠራል፡፡ (ኤር17÷21)
ሥራ መሥራትን የሚከለክለው ሕግ የተደነገገው የሰንበት ቀን የአምልኮ፣ የጸሎትና የዕረፍት ቀን እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡
ሆኖም ግን የአይሁድ ረበናት (መምህራን) በርካታ ጥቃቅን ሕግጋትን በመጨመር በመጀመሪያ የነበረው የሰንበት ቀን ትርጉም እንዲጠፋ አደረጉ፡፡ ከእነዚህም ጥቃቅን ሕግጋት የተነሳ በሰንበት ቀን በሽተኛ መፈወስም ሆነ መልካም ሥራ መሥራት አይቻልም ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የ38 ዓመት በሽተኛን በመፈወስ በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት እንደሚቻል አስተመረ፡፡ (ማር2÷23)
የ38ቱ ዓመት በሽተኛ ግን የሰንበትን ሕግ ያፈረሰው ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ እኔ አይደለሁም በማለት ክርስቶስን ወነጀለው፡፡ ለአይሁድ መሪዎችም አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለኝ እርሱ ነው አላቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክርስቶስ የተፈወሰውን በሽተኛ አገኘውና ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ አለው፡፡
ከዚህ እንደምንረዳው የዚህ ሰው ህመም የመጣው በኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ ሰውየው በኃጢአቱ ጸንቶ የሚቀጥል ከሆነ ከዚህ የባሰ ክፉ ነገር እንደሚደርስበት ኢየሱስ ክርስቶስ አስጠነቀቀው፡፡ ማለትም በመጨረሻው የፍርድ ቀን ተኮንኖ የዘላለም ሞት ይፈረድበታል፡፡
የተፈወሰው በሽተኛ ውለታ ቢስ ነበርና፡፡
እኛም በበኩላችን ከዚህ ታሪክ የምንማረው ለተደረገልን ቸርነት ሁሉ እንደ ቅዱስ ዳዊት ምስጋና ማቅረብ እንጂ እንደ መጻጉዕ ውለታሚሶች መሆን አይገባንም፡፡