ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሥራ ጉብኝት አደረጉ

2438

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት  ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን  የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሐሙስ ሰኔ 18 /2007 ዓ.ም የቢሮ ውስጥ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከቀኑ 10 ሰዓት ሲሆን  ከሀገረ ስብከቱ ዕቅድና ልማት  ክፍል ዋና ክፍል ኃላፊ  ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ  ጋር በመሆን  ለሥራ ጉብኝት ላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ የደብሩን አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ተክለ ማርያም መንገሻን ጨምሮ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የልማት ኮሚቴዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች በቦታው በመገኘት አቀባበል አደርገውላቸዋል፡፡
በመቀጠልም የደብሩ አስተዳዳሪ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ በደብሩ በመሠራት ላይ ያሉ እና ሊሠሩ የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በአካል በማሳየት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወደ ላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ለሄደው ልዑክ ገለጻ አድርገዋል፡፡  ሊቀ ብርሃናት ተክለ ማርያም  መንገሻ  በደብሩ  በመሠራት ላይ ያለውንና ሊሠራ የታቀደውን የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ  ለሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ በሚያስረዱበት ወቅት  በተለይ  ትኩረት ሰጥተው በጋለ ስሜት ሲናገሩ የነበረው በደብሩ በአምስተኛው ፓትርያርክ  በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ስም ተሰይሞ የአካባቢው ሕፃናት እየተማሩበት የሚገኘው ከመዋእለ ሕፃናት እስከ ሦስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ  የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ትምህርት ቤት የልማቱ አንዱ አካል በመሆኑ  በቅርቡ እስከ ስምነተኛ ክፍል ድረስ ባለው የትምህርት ዘርፍ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት እና ለዚሁም ጉዳይ የደብሩ ሰበካ ጉባኤና የልማት ኮሚቴው ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ   መሆኑን  አስምረው ተናግረዋል፡፡
የላፍቶ ደብረ ትጉሃና ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን  ከ76,000 ካሬ ሜትር በላይ  ሕጋዊ የሰነድ ማረጋገጫ ያለው የመሬት ይዞታ ያለው ሲሆን በዚህ መሬት ላይ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የልማት ኮሚቴ  የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ በመያዝ አመርቂ ሥራ ለመስራት ቆርጦ መነሣቱን  የሰበካ ጉዳኤው ምክትል ሊቀመንበር እና  የደብሩ የልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር   በሚያብራሩበት ወቅት  በቅርብ ጊዜ ከሚሰሩት መካከል  የተወሰነውን መሬት  በጨረታ አውዳደሮ በማከራየት ከኪራዩ በሚገኘው ገቢ የቤተክርስቲያኑን  ግቢ አስፓልት  ማንጠፍና አውደ ምህረቱን በተለይ በሸክላ ለመሥራት የታሰበ ሲሆን ይኸውም ተጀምሮ በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  አያይዘውም የአብነት ትምህርት ቤት   ይሠራበታል ተብሎ የታሰበውን ቦታ  ለዋና ስራ አስኪያጁ እና ከሀገረ ስብከቱ ለሄደው  ልዑክ  አስጎብኝተዋል፡፡ 
በሁለተኛ ደረጃ በደብሩ ከሚሰሩት የልማት ሥራዎች መካከል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ስም ተሰይሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለውን ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ከዚያም እስከ አሥረኛና አሥራ ሁለተኛ ክፍል የማድረስ ሲሆን ይኸውም ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ጋር ፕሮሰስ   ተጀምሯል ብለዋል፡፡ 
የረጅም ጊዜ እቅድ ተብሎ በደብሩ የልማት ኮሚቴ እቅድ ውስጥ የተካተተው ደግሞ ቤተክርስቲያኑ ባለው ሰፊ የመሬት ሀብት ላይ ሁለገብ የሆነ ዘመናዊ ሕንፃ በመሥራት  የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ገቢ ለመደጎም ያገለግላል ተብሎ  የታሰበ መሆኑን  አስረድተዋል፡፡      
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ብርሃን  ዘመንፈስ ቅዱስ  ይህን ሁሉ ዙረው ካዩና  ከደብሩ አስተዳዳሪ እንዲሁም  ከሰበካ ጉባኤ አባላት እና የልማት ኮሚቴው የተሰጠውን መግለጫ ከሰሙ በኋላ የሚከተለውን የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
1.የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የልማት ኮሚቴ  ለቤተክርስቲያን  ዕድገት  እያደረጉ ያለውን ጥረት በማድነቅ በግቢው ሊሠራ የታቀደው የአብነት ትምህርት ቤት ተተኪ መምህራንን  በማፍራት ለቤተክርስቲን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ  ግንባታው በቶሎ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሀገረ ስብከቱ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡
2.በብጹዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ስም የተሠየመው ትምህርት ቤት  የሚሰጠው አገልግሎት  ዘርፈ ብዙ ነው፡፡  ምክንያቱም ከትምህርት ቤቱ የሚገኘው ገቢ  በደብሩ ለሚሰራው የልማት መፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን ትልቁ ጥቅም ግን በአካባቢው የሚገኙ ክርስቲያኖች ልጆቻቸው ከዓለማዊው ትምህርት ጎን ለጎን የቤተክርስቲያን  እውቀት የሚገበዩ በመሆናቸው ትምህርት ቤቱ ቤተ ክረሲያናችን አልፎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የልማት እና እድገት እቅድ  የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
 ስለዚህ በታቀደው መሰረት ለተፈጻሚነቱ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የአስተዳደር ጽ/ቤቱ እና የልማት ኮሚቴው   በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው  አሳስባለሁ በማለት የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡   
  በመጨረሻም በዚህ ደብር እየተሠራ ያለው የልማት ሥራ የመልካም አስተዳደር ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም  መልካም አስተዳደር በሌለበት ሰላም፣ ሰላም በሌለበት ልማት  የሚታሰብ አይደለምና ነው በማለት  የላፍቶ ደብረ ትጉሀን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ  ከልማት ሥራው ባሻገር በደብሩ ያለው መልካም አስተዳደርን የሚያስመሰግነው  ነው በማለት ከተናገሩ በኋላ  የመስክ የስራ ጉብኝታቸው በጸሎት ተጠናቋል፡፡
  በተያያዘ ዜና በሀገረ ስብከቱ ዕቅድና ልማት ክፍል ዋና ክፍል ኃላፊ  ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ አሳሳቢነት ወደ ማህደረ ስብሀት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔአለም ቤተክርስቲያን ጉዞ ተደርጎ  በዚያም ዲያዛይን ተሠርቶለት በቅርቡ በደብሩ ቅጽረ ግቢ ሊሠራ የታቀደውን ሁለገብ ዘመናዊ አዳራሽ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥኡመ ልሳን ኪ/ማርያም  ተገኝተው  ለዋና ሰራ አስኪያጁና ከሀገረ ስብከቱ ሌደው ልዑክ ስለሚሠራው ሁለ ገብ አዳራሽ(ሕንፃ) ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ሊቀ ማእምራን  የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ   በአጠቃላይ በደብሩ  በመከናወን ላይ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በመጎብኘት እና የሥራ መመሪያ በመስጠት የእለቱን  የመስክ የሥራ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል፡፡

{flike}{plusone}