ለእድገትእንነሣ

እድገት ከታች የሚጀምር ሆኖ ወደ ከፍታ የሚምዘገዘግ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፡፡ እድገት ዝም ብሎ አልጋ በአልጋ የሚመጣ የምኞት ውጤት ሳይሆን የዕውቀት፣ የጉልበት፣ የጊዜና የሕይወት መስዋትነትን የሚያስከፍል የተጋድሎ ውጤት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክንውን ውስጥ እድገትም ሆነ ተቃራኒ ጉዞውን አመላካች የሆኑ ክስተቶች የግድ ይኖራሉ፡፡ እድገት በተለያየ ሁኔታና መልክ የሚገልጽ ቢሆንም መንፈሳዊ እድገት፣ አዕምሯዊ እድገት፣ አካላዊ እድገትና ልማታዊ እድገት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እድገት መለወጥ ነው፡፡ ለውጥ በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ የተለወጠ ማንነት የተለወጠ አመለካከትና አስተሳሰብ እንዲሁም የተለወጠ የአሰራር እንቅስቃሴ ልንመለከት ይገባል፡፡ የሰው ልጅ ከዘመኑ ጋር የሚሄድና ጊዜውን የዋጀ የአመለካከትና የአስተሳሰብ እድገት ካላስመዘገበ የጉዞውን ትክክለኛነት መፈተሽ ይገባዋል፡፡

እድገት በአንድ አቅጣጫ የሚለጠጥ በሌላኛው ደግሞ የሚሟሽሽ ክፍለ እንቅስቃሴ ሳይሆን ሁሉንም የእድገት ለውጦች ያካተተ ሁለንተናዊ ለውጥ ነው፡፡ መወለድ እስካልቆመ ድረስ ተፈጥሯዊና መንፈሳዊ እድገት እንዳለ ሁሉ ለአንድ መሰረታዊ ዓላማ ይዞ የተመሰረተ ማንኛውም ተቋም በተቀመጠለት የእድገት ፍጥነትና እርከን የተቋሙን እሴት፣ የተቋሙን ዓላማና ራዕይ ጠብቆ የመንቀሳቀስና የማደግ፣ የአሰራር መመሪያዎችንና ደንቦችን የማውጣትና የማስፈጸም፣ ሕብረተሰቡን የማገልግል፣ የዘመኑን አስተሳሰብና አመለካከት በማጥናት ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ተቋማዊ አስተሳሰብና ሰላም የማስፈን፣ ለእድገታዊ ለውጥ መነሳትና አመርቂ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ የግድ ይሆንበታል፡፡ ምክንያቱም መሰረታዊ ዓላማና የተቀመጠ ራዕይ የሚለካ እሴትና የአሰራር መመሪያዎች የሌሉት ብሎም እድገት የሚያስመዘግብ ተቋም እጣ ፋንታው ሰራተኞችን መበተን ወደ መቃብርም መውረድ ይሆናልና ነው፡፡ እድገት በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የመነቃቃት፣ የመነሳሳትና የመለወጥ እንዲሁም ክፍተቶችንና አሰራሮችን የመፈተሽ፣ በሚያዋጡ አሰራሮች የመቀየር የአመራር ብቃታዊ ውጤት ሲሆን እድገቱም ዘርፈ ብዙ ደግሞም ሁለንተናዊ ነው፡፡ ተፈጥሯዊም ሆነ መንፈሳዊ እድገት የደረሰበትን የእድገት ጣሪያ የሚለካባቸው መስፈሪያዎች እንዳሉ ሁሉ የአንድ ተቋም ልማታዊ እድገትና ያመጣው ለውጥ የሚፈተሽበት የራሱ የሆነና የተቀመጠ መርሃዊ መስፈርት አለው፡፡ ከዚህ የመለኪያ መስፈርት ሞልቶና ተርፎ ከተገኘ ትርፍማነቱን ሲያመላክት ከጎደለ ግን በኪሳራ ውስጥ ያለ፣ራሱን መፈተሽ የሚገባው ካልተሳካም የመቃብር አፈሩን በራሱ ላይ የበተነ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡

የኢ/ኦ/ቤ/ክያን ቀደምት ከሚባሉ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ እንደመሆኗ መጠን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም ለግዙፉ ዓለማችን ያበረከተችው አስተዋጽዖ የትየለሌ ነው፡፡ ከሰዎች አስተሳሰብና የአመለካከት እድገታዊ ለውጥ ጀምሮ እስከ ሥነ-ጥበብ እና ሥነ-ፅሁፍ እድገት ድረስ የተመዘገበው ሁሉ በቤተክርስቲያናችን ያላሰለሰ ጥረት መሆኑን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ከተዋቀሩ የቤተ-ክርስቲያናችን መምሪያዎች መካከል አንዱና ዋንኛው የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ነው፡፡

አዲስ አበባ ሃ/ስብከት ከአሁን በፊት ያስመዘገባቸው በርካታ ዕድገት ቢኖሩትም አሁን ደግሞ ለእድገት መሰናክል የሆኑበትን አሰራሮችና ክፍተቶች ጊዜ ወስዶ በመመርመርና በማጤን የእድገት ግብዓት የሚሆኑ አዳዲስ አስራሮችንና አመለካከቶችን በሥራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል የእቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠትና የሚማሩበትን የትምህርት እድል በማመቻቸት የሰው ኃይሉን ማጠናከር፣ የጡረታ ሪከርድ ክፍል በመክፈትና በአዲስ የሰው ኃይል የመመሰረት፤ የወንጌሉን የድምፅ ከፍታ ለመጨመር በአዲስ መልኩ የተዋቀረውን የሚዲያ ክፍል በመጠቀም ተከታታይ የሆኑና ዓምዳቸውን ጠብቀው የሚሄዱ ትምህርቶችን፣ ወቅታዊ የቤ/ክያናችን ጉዳዮችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን፣ መንፈሳዊ ወጐችንና መጣጥፎች በማካተት በመንፈሳዊ ጋዜጣ መጽሔት በርካታ የሆኑ ተከታዮች ባሉት ድህረ-ገፅም ጭምር በማዘጋጀት ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሰራጭም በማድረግ፣ የቤተክርስቲያናችን የህልውና መሰረት ስብከተ ወንጌል ስለሆነ ሀ/ስብከቱ አደግድጎና ወገቡን ታጥቶ ከቅዱስ አባታችን መመሪያን በመቀበል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እና በመተባበር አብሮ በመስራት የአንድነት ጉባኤዎችን፣ ልዩ የወንጌል መርሐ ግብሮችን በራሱ በማዘጋጀት እና እንዲዘጋጁ በማድረግ የዕድገት ጎዳናውን ጥርጊያ ለማሳየትና የአንባሳውን ድርሻ ለመውሰድ ዝግጅቱን ጨርሶ “ኑ ለእድገት እንነሳ” የሚለውን መሪ ቃል በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ለእድገት እንነሳ ስንል የሀገረ ስብከታችንን ብሎም የቤተክርስቲያናችንን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅና ሁለንተናዊ እድገቷን ለማፋጠን በጋራ እንስራ፣ እንወያይ፣ እንተባበር ድርሻችንን እንወቅ ማለታችን እንደሆነ ተረድተን በሀገረ ስብከታችንና በክ/ከተማ ጽ/ቤት ያላችሁ የሥራ ባልደረቦች፣ በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የምታገለግሉ አስተዳዳሪዎች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ አገልጋይ ካህናትና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በእድገት እንንነሳ የሚለውን የሀገረ ስብከቱን ጥሪ ሰምታችሁ ቤተክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንድናሳድጋትና በከፍታ ማማ ላይ ከፍ ብላ እንድትታይ የበኩላችንን እንወጣ፡፡ የቅዱስ አባታችን ፀሎት አይለየን!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር