ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ከሀገረ ስብከቱ እና ክ/ከተማ ሠራተኞች ጋር ትውውቅ አደረጉ
በመ/ር ኪዱ ዜናዊ እና በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ዛሬ ሐምሌ 09/2010 ዓ.ም በኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ ከብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ የመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ጉዳይ የበላይ ሐላፊ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍለ ከተማ ሠራተኞች ጋር ትውውቅ ካደረጉ በኋላ የሥራ አመራርም ሰጥተዋል፡፡
የዛሬ ዓመት ሐምሌ 09/2009 ዓ.ም በዓለ ሲመታቸው እንደነበረ ያወሱት ሊቀ ጳጳሱ ፣ በዘንድሮ ደግሞ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ለአገልግሎት መሾሜ እግዚአብሔርን አመስግነዋለሁ በማለት በታማኝነት፣ በቅንነትና በመንፈሳዊነት ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሌሎች አሁረ ስብከት ለየት የሚያደርገው የሀገራችን መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ ሀ/ስብከት እንደመሆኑ መጠን ብዙ የዲፕሎማትና ሙሁራን የሚገኙበት በመሆኑና ብዙ ውስብስብ የሆኑ አሠራር ያሉበት ሀ/ስብከት ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
ብዙዎች አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከባድ ነው ጠንቀቅ ይበሉ ቢሉም ሥራው ለእኔ አዲስ ስላልሆነ የ50 አህጉረ ስብከት ችግሮቻቸውና ፈተናቸውን አስቀድሜ ስለማውቅ ችግሩን ለእኔ አዲስ አይደለም ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሲስተም ችግር እንጂ ከሌሎች የተለየ አይደለምበማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ የገንዘብ ማዕከል በመሆኑ ለሙስናና ለተለያዩ ሰብአዊ ችግሮች የተጋለጠ ስለሆነ ነው እንጂ የተለየ ሥራ ኖሮት አይደለም፡፡ ከባድም አይደለም፣ ከባድ የሚያሰኘው አሠራሩ ነው በቅንነት ካሰብነው ግን እጅግ በጣም ቀላልና ማስተካከልና ማረም የሚቻል ሀገረ ስብከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ መስመር ማስያዝ ቀላል ቢሆንም ቅንነት ግን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ስላለፉና ስለነበሩ ሰዎች መፈረጅ አግባብ የለውም፣ እኔ በኔ ልቡናና ጭንቅላት ማሰብና መሥራት አለብኝ እንጂ በሌሎች ልቡናና አእምሮ አላሰብም፡፡ በሞኝነት ሥራ ተሠርቶ ከሆነ በኔ ዘንድ አይሠራም፡፡ ይህ ብልሹ አሰራር በዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ እንዳለም አይሰራም፡፡ በእውነትና በማስተዋል እንሰራለን እንጂ በማለት ተስፋ ሰጪነት በተሞላ ቃላት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
አድልዎ ማድረግ ጸያፍ ነው፡፡ ዓለም ከተውን በኋለ ተመልሰን ዓለማዊ መሆን አይገባንም፣ ስለዚህ በኔ ዘንድ አድልዎ፣ ብሄርተኝነት፣ ለያይቶ ማየት የለም፣ ሁሉን በእኩል ዓይን እናያለን፣ ዘረኝነት መናፍቅነት ነውና ከቤተክርስቲያናችን ማስወጣት ነው ያለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንዱ ለአነዱ ማጥቃትና የጉሩብ ሥራ አስያፈልገንም፣ እናስቀረዋለን፡፡ አገልጋዮች ባላቸው ሙያ፣ ችሎታና አቅም በማስተካከል እንሰራለን፣ በእቅድም እንሠራለን፡፡ የአብነት መምህራን የሚገባቸው ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ እናደረጋለን፡፡ የተመራ ደብዳቤ ሳይዘገይ ወዲያውኑ እንዲወጣ፣ ሁሉ በወቅቱ ሰዎች ሳይጉላሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እናደርጋለን ካሉ በኋላ እስከ አዲስ ዓመት አዲስ ቅጥርና ዝውውር የሌለ መሆኑን ከዚህ ይልቅ የተፈናቀሉ ሠራተኞች የማሰተካከል ሥራ የምንሠራ መሆኑንና በአዲስ አመት በአዲስ መልክ የምንጀመር መሆኑን እንድታውቁልን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች በሰዓታቸው ገብተው በሰዓታቸው እንዲወጡ መመሪያ በማስተላለፍ እኔ አመራሩን፤ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ ደግሞ ማናጅመንቱን እንሠራለን በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለም አንድ ሰው ሥራ አስኪያጅን ለማግኘት ብዙ ጊዜ መፍጀት የለበትም፤ሥራዎቻችንን በአግባቡ ከሠራን ችግሮችን መቅረፍ እንችላለን፡፡ የጥበቃ ሠራተኞች ሁሉን በእኩል ዓይን ማስተናገድ አለባችሁ ካሉ በኋላ በቅርቡም ወደ ታች ወርደው ከክፍለ ከተማ አገልጋዮች ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል፡፡