ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ለ፳፻፲፰ ዓ/ም ዐዲስ ዓመት የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ተካሔደ
የ፳፻፲፰ ዓ/ም ዐዲስ ዓመት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ተካሔደ።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ተሃይማኖት፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣ የየመምሪያውና የድርጅት ሐላፊዎች፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ዋና ጸሐፊዎች፣ የታላላቅ ገዳማት አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መምዘራን፣ የምስካየ ኅዙናን አገልጋዮችና የተምህሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ፣ የጋሞ ማኅበረሰብ ኦርቶዶክሳውያን መዘምራን ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ እንኳን ለዘመነ ማርቆስ ፳፻፲፰ ዓ/ም በመንበረዎ አጽንቶ በጤና ጠብቆ በሰላም አደረሰዎ በማለት በጋራ የመልካም ምኞት መግለጫ መልእክት አስተላለፈዋል።
አስተዳዳሪዎቹ አክለውም በመልእክታቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፕትርክና ዘመናቸው ጥበብና አባታዊ ስክነት ምን እንደሚመስል በመግለጽ አድንቀው አቅርበዋል።
አያይዘውም ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ብሎም ለዓለም ሰላም የምትጸልይ በመሆኗ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሥርዐትን መሠረት ባደረገ መልኩ በውይይትና በዕርቅ በመፍታት እንደሀገርም ለሰላም አብዝቶ ለመሥራት ቃል የሚገባበት ዐዲስ ዘመን በመሆኑ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ትክረት እንደሚሰጠውና ሁነኛ ለውጥ እንደሚመጣም ተስፋቸውን በመግለጽ መልእክት አስተላልፈዋል።
በማስከተልም በሊቃውንት በሰንበት ትም/ቤት መዘምራንና በጋሞ ማኅበረሰብ ኦርቶዶክሳውያን መዘምራን ዝማሬ ቀርቧል።
በቀጠልም ቅኔያት በታላላቅ ሊቃውንት ቀርበዋል።
ለዐዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሰዎ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስነታቸውን የፕትርክና ዘመናት ብዙ ውስብሰብ ችግሮች የተከሰቱበት ቢሆንም በመልካም የአባትነት መሪነትና ትዕግስት በማለፍ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረዎ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስነታቸው ጸሎትና መሪነት በመታገዝ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ትኩረት ተሠጥቷቸውን ሊሠሩ ስለታሰቡ አጀንዳዎች ጠቁመዋል።
1.ስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእጅጉ ማጠናከር
2.የቤተ ክርስቲያን አንድነት በውይይትና በዕርቅ መፍታት
3.የራስ አገዝ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር
4.የብዙኃን መገናኛ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ልማት (ሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች) ዘመኑን በሚጠይቀው ፍጥነትና በቤተ ክርስቲያን በሚመጥናት አሠራርን ማዘመን የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል።
አክውም ከዚሁ ጋር የሀገረ ሰላም ትውልደ ተኮር ሥራዎች ከፍተኛ ትክረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ያስታወሱ ሲሆን ለዚህም የቅዱስነታቸው አባታዊ ጸሎትና ቅን መሪነት እንዲሁም የብፁዓን አባቶች ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የኔባይነትና ድጋፍ ትብብር እንደማይለያቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በበኩላቸው የአንዷን ትልቋን ቤተ ክርስቲያን ሥርዐቷንና ትውፊታን በማክበር ይህን የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ላዘጋጁና በተገባው ነገር ሁሉ ለደከሙ ለተሳተፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል እግዚብሔር ይባርካችሁም ብለዋል።
ቀጥለውም ዐዲስ ዘመን ዐዲስ ሕይወት፣ በንስሐ ልቡን ያዳላደለና መሻቱን ሁሉ ለእግዚአብሔር አሳልፎ የሰጠ ልብ የሚፈልግ በመሆኑ ሁላችንም ዐዲሱን ዘመን የቀንና ቁጥሮች መለወጥ እንዳይሆን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል።
ለዐዲስ ዘመን ራሳችንን ስናዘጋጅ የሀገረ ሰላም የወገኖች ሕይወት፣ የወንድማማችነት ኑሮ ያሳስበናል በመሆኑም በዘመመውና በጎደለው በኩል ለመሙላትና ከመፍትሔው ጎን ለመሰለፍ የተዘጋጀን መሆን ይኖርብናል ብለዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና አበምኔቶች ያስተላላፉትን የእንኳን አደረሰዎ መልእክት አመስግነው የመልካም ዓመት አባታዊ ምኞታቸውን በመግለጽ መርሐ ግብሩን በጸሎትና በቡራኬ አጠናቀዋል።
