ለቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ የወሰን ችካል ለመቸከል በትናትናው ዕለት ተይዞ የነበረው መርሐ ግብር መስተጓጎሉ ተገለጸ።

ለቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ የወሰን ችካል ለመቸከል በትናንትናው ዕለት ተይዞ የነበረው መርሐ ግብር መስተጓጎሉ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ ቦታ አቅርቦት እንዲዘጋጅላቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሚያዚያ 5/2013 ዓ/ም ከተወሰነላቸው የቦታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንደነበር ሰነዱ ያስረዳል።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ከተማ አስተዳደሩ የቦታ አቅርቦቱ እንዲዘጋጅ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ እንዲፈለግ መመሪያ ያስተላለፈ ሲሆን ከብዙ ጥረት በኋላ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በለቡ መርጡለ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ 25883.5 ካሬ ሜትር በመንግሥት ተፈቅዶ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ” በሚል ስም ተዘጋጅቶ ጉዳዩን ለሚከታተለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰጠቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህን ተከትሎም የቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ የወሰን ችካል ለመቸከል ቢሞከርም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ የቀረ መሆኑም ተገልጿል።
ከብዙ ድካም በኋላ በትናንትናው ዕለት በተያዘው የወሰን ችካል መቸከል መርሐ ግብር መሠረት የሚመለከታቸው የአካላት የሀገረ ስብከቱ የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ሐላፊ መምህር ኀይሉ ጸጋውና ሌሎች የክፍለ ከተማውና የወረዳው ተወካዮችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ያነሱ አካላት በፈጠሩት የጸጥታ ችግር ምክንያት አንድ የሀገረ ስብከት ሠራተኛ መጠነኛ ጉዳት ሲደርስበት በሌላው የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኀላፊ ለመደብደብ ሙከራ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
የጸጥታው ችግር ሲፈጠር የጸጥታ አስከባሪዎች በቦታ የነበሩ ሲሆን የሚችሉት ሁሉ በማድረግ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከላቸውን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች መረጃውን አድርሰውናል።
ቆይቶም የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር የጸጥታ አስከባሪዎች ጥያቄዎችን በሕጋዊ መልክ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል መጠይቅ እንደሚገባ አሳስበው በይቅርታ እንዲፋታ ሆኗልም ተብሏል።
የሚመለከተው አካል ለማነጋገር ወደ ሥፍራው ያቀኑት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ቦታውን በመመልከት በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከተው አካል እንደሚያነጋግሩ ተናግረዋል።
አክለውም ችግሩን በሰላማዊና በሕጋዊ የሚመለከተውን የመንግሥት አካል መጠየቅ ሲቻል ከሕግ ወጭ በሆነ መልኩ ኀይልን በመጠቀም መርሐ ግብሩን ማስተጓጎል አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሀገረ ስብከቱን የሥራ ሐላፊዎች ከከፍተኛ ጉዳት ያዳኑት የመንግሥት ጸጥታ አካላትን አመስግነዋል።
በቀጣይ ችግሩን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር በመፍታት በቅርብ ቀን የቅዱስ ያሬድ የዜማ ኮሌጅ የወሰን ችካል ተጠናቆ የመሠረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሀገረ ስብከቱ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንን አስታውሰዋል።