ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሣት የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

መላው ኢትዮጵያውያን ዕድሜ ጠገብ የአገር ቅርስ ለሆነው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዕድሳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ካቴድራሉ ጥሪ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡

የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ካቴድራሉ ከተገነባ ለረጅም ዓመታት ሳይታደስ በመቆየቱ በጣሪያው ላይ የመሰንጠቅ አደጋ ደርሶበት ውሃ እያፈሰሰ ይገኛል።

ካቴድራሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በቅርስነቱ በርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙትና ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የቆዬ ነው። ለአገራቸው ታላላቅ ሥራ የሠሩ አርበኞችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያንን በክብር በማሳረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ካቴድራል በመሆኑ ለቅርሱ ዕድሳት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የካቴድራሉ ሕንጻ ዕድሳት ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተድላ ተሾመ በበኩላቸው፤ የካቴድራሉ ሕንጻ ከፍ ባለ ጥራትና በውጭ አገር ባለሙያዎች የተገነባ ነው፡፡ ቅርሱ ከተገነባ ረጅም ዓመታት እንዳስቆጠረ ጠቁመው፤ ከተገነባ ጀምሮ ሥር ነቀል ዕድሳት ስላልተደረገበት ከፍ ያለ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ዕድሳት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጅነር ሥርዓት አየለ እንደገለጹት፤ ሥራውን ለመጀመር የደረሰውን ጉዳት ማጥናት በማስፈለጉ በዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት ተደርጓል፡፡ ካቴድራሉን ጥንታዊነቱን በጠበቀ መልኩ ለማደስ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በተለይ በሕንጻው ጣሪያ ላይ የመሰንጠቅ አደጋ ደርሶበት ውሃ እያፈሰሰ መሆኑንና በሌሎች የሕንጻው አካላት ላይም የተለያዩ ጉዳቶች በመኖራቸው አስቸኳይ ዕድሳት እንደሚያስፈልገው በጥናቱ መመላከቱን ተናግረዋል፡፡

ከዕድሳት ሥራው ጋር ተያይዞ የካቴድራሉ ምድረ ግቢን የማስዋብ ሥራም እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ተያያዥ ወጪዎችን ሳይጨምር በሕንጻው አካል ላይ ብቻ ለሚደረገው ዕድሳት ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ብር ሊፈጅ እንደሚችል መገመቱን አስረድተዋል፡፡

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአጼ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት በ1924 ዓ.ም ተገንብቶ ላለፉት 90 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ከካቴድራሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሣሣይ የመርካቶ ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሁለገቡ ሊታደስ መሆኑን ከሰሞኑ መዘገባችን ይታወሣል።

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

መረጃው
ከኢኦተቤ የፌስቡክ ገጽ የተገኘ

በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ