ለመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተክርስቲያን ሕንጻ ዕድሳት መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የዕድሳቱ ትርጉም ሃይማኖትን፣ ታሪክንና ሀገራዊ ዕሴትን ለትውልድ ማሻገር ነው።
ለመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) ሕንጻ ዕድሳት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቋል ። እድሳቱ ከ157 ሚሊየን ብር በላይ ይጠይቃል የሚል የባለሞያ ጥናት ቀርቧል።
ታሪክን ለትውልድ ማሻገር ተራው የእኔ ነው በሚል መሪ ሐሳብ ለመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) ሕንጻ እድሳት እየተካሄደ ነው።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ክብሩ ገብረ ጻድቅ እንደገለጹት የሀገር ቅርስ የቤተ ክርስቲያኗ ኃብት ለሆነው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) ዕድሣት ሁሉም ኢትዮጵያውዊ ድጋፍ ሊያደረግ ይገባል።
እድሳቱን ለማስጀመር ጥር 18 ታቦተ ሕጉ ወደ መቃኞ መግባቱን ጠቅሰው፤ ግንቦት ወር የዕድሳቱ ሥራ መጀመሩንና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕንጻውን ዕድሳት ለማጠናቀቅ መታቀዱንም መልአከ ገነት ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቅርሱን ጠብቆ እድሳት እንደሚደረግለት በመግለጽ፤ ሁለተኛውና ሦስተኛ ምዕራፍ ደወል ቤት ክርስትና ቤት ቤተልሔም ሙዚየምና የግቢው እድሳት እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።
የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች የእየተዘጋጁ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በአጽዋማት ወቅት ቁርሳችንን ለቤተክርስቲያናችን ዕድሳት፣ ጉባኤዎች፣ የቤተሰብ ጥየቃ፣ የኦንላይን ገቢ ማሰባሰቢያዎች እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል።
ዕድሳቱ ከ157 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚፈጅ ጠቅሰው፤ ለኮንትራክተሩ እስካሁን 20 ሚሊየን ብር ክፍያ መፈጸሙን ጠቁመዋል።
ሚሳክ ጀነራል ኮንስትራክሽን የድርጅቱ ተወካይ ኢንጅነር ነብዩ ደምሴ በበኩላቸው ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ የቀደምት አባቶች ኪነ ሕንጻ ዕውቀት የታየበት ለዚህም እድሳቱ ጥንቃቄም ይጠይቃል!!
የሕንጻ እድሳቱ ከተጀመረ ሁለት ወራት እንደሆነው ጠቅሰው እስካሁን 20 በመቶ መሰራቱን ገልጸዋል።
እድሳት ከመጀመሩ በፊት ጥልቅ ጥናት መደረጉን በመግለጽ ሕንጻ እድሳቱ ቅርሱን በጠበቀ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ቅርስ እጃችንን በመዘርጋት ታሪክን ጠብቀን ለትውልድ እናሻግር።