ለመምህር ይቅርባይ እንዳለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው
በቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ/ም በዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመደቡትን መ/ር ይቅርባይ እንዳለንና ምክትላቸውን መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐናን በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የአቀባበል መርሐ ግብር ተደረገላቸው፡፡
ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ሌሎችም ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤ የክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ሐላፊዎች፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሪዎችና ጸሐፊዎች በተገኙበት በተደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ብፁዕ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሹመት ደብዳቤውን በንባብ ካሰሙ በኋላ ² ልጁ የእኛው ጽ/ቤት የሥራ ባልደረባና አስተዋይ ልጅ ነው ፤በዛሬ ቀን ደግሞ ሙሽራ ስለሆነ እኛ የእርሱ አጃቢ ሚዜዎች ሆነን በዚህ ተገኝተናል በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን ጀምረው በአሁኑ ጊዜ መሆን ሰለሚገባው አሠራር ሲገልጹም በአለንበት በዚህ ወቅት ቤተ-ክርስቲያናችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፤ በሩን ለባለጉዳዮች ክፍት አድርጉ ነገር ግን የጊዜውን ሁኔታ ለራሱ ለጊዜ እንተውለት ጊዜ ራሱ በጊዜው ይናገራል በሚል ተጨማሪ በሳል ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡ የቅዱስ ፓትርያሪኩን መልእክት ያስተላለፉት የጽ/ቤቱ የውጭ ግንኙነት የበላይ ሐላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊም በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ የተሾማችሁ ሹመኞች የተጣለባችሁን ታላቅ አደራ በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ሐላፊዎችና ሌሎችም የሥራ ባልደረቦች ጋር በመመካከርና በመነጋገር ትሠሩ ዘንድ አደራ እንላችኋለን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዚሁ ደማቅ የአቀባበል መርሐ ግብር ንግግር ያደረጉት አዲሱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ ሀገረ ስብከቱም ብሎም ቤተክርስቲያኒቱ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢና ለክብሯ የማይመጥን ከመሆኑም በላይ በዓለማውያን የትችት መድረክ እንደ አንድ አጀንዳ መሆኗን ገልፀው የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነትና ክብር ለመመለስ ፤ እየታየ ያለውን አስተዳደራዊ ክፍተት ለማስተካከል፤ ቀኖናና አስተምህሮዋን ለመጠበቅና ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ጠንክሮና ተግባብቶ መሥራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ገልፀው ለሚጠብቋቸው በርካታ የቤት ሥራዎችን ለማሳካትና አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በጸሎትና በሐሳብ ይታገዙ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሙሉ ንግግራቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጋምቤላና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ የምሥራቅ ወለጋ፣ የሆሮጉድሩ እና የቄለም ወለጋ ሊቀ ጳጳስ፤
የመ/ፓ/ጠ ቤ/ክ የየመምሪያ ሐላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ሐላፊዎች እና ሠራተኞች የአድባራት እና ገዳማት አለቆች እንዲሁም ጸሐፊዎች በዚህ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኛችሁና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶቻችን በሙሉ ፡፡
በቅድሚያ እንዲህ አምራችሁና ተውባችሁ በሙሉ ፍላጎትና በውስጣዊ ደስታ ተሞልታችሁ ይህንን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ለማሳመር በዚህ ሥፍራ በመገኘታችሁና በዚህ ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእርጋታ ሆናችሁ ሰላምን ለማስፈን ላሳያችሁት መንፈሳዊ አባትነታችሁ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን በልዑል እግዚአብሔር ስም አቀርባለሁ፡፡በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጣም በርካታ ካህናትን ያቀፈና ባለ ብዙ ችግርም ጭምር በመሆኑ ምርጥ የሥራ ተሞክሮዎች እንዳሉ ሁሉ ብዙ የሥራ ውድቀቶችም አሉት፡፡ ምንም እንኳ ሥራው አስቸጋሪ ባይሆንም ነገር ግን ከሥራው ጋር ተያይዞው የሚመጡ የግለሰቦች ጠባይ ሥራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው መገመት አያዳግትም፡፡
ይሁን እንጂ በጋራ ሆነን ሳንበጣጠስ፣ ሳንለያይ ሳንገፋፋ፣ ዘርና ጎሳ ሳንቆጥር አብረን በጋራ ከሠራን፤ ከተመካከርን እኔ ከበላሁ ሌላው ጦሙን ይደር የሚለውን የሆዳሞችን አመለካከት ከተውን እንዲሁም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው የአህያይቱን አባባል ከተጸየፍን እንኳን ለእኛ የሚሆን ሰላም ለዓለም የሚበቃ ሰላም ይኖረናል፡፡ አሁን የምናየው ሁኔታ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ብቻም ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ እና ከመንፈሳውያን አባቶችና ወንድሞች ቀርቶ ከዓለማውያን ሰዎች እንኳን የማይጠበቅ ተግባር በመሆኑ እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፤ ቤተክርስቲያናችንንም ዋጋ እናስከፍላታለን፡፡
ቤተክርስቲያናችንን መለወጥ ከፈለግን የተማሩ ሊቃውንት ይከበሩ፡፡ ከውሻ ጋር ታግለው ቁራሽ ለምነው የተማሩት ትክክለኛውን የምዕመናን ፊት እየገፋቸው ከተማሩት ሊቃውንት በላይ ሆነው የሚኖሩበት ጊዜ ያብቃ፡፡ ሰዎች በሚጠቀሙት ቁሳቁስ እና በሚለብሱት ልብስ አይመዘኑ፤ በአፈ ጮሌነትም አይከበሩ፤ መጽሐፍ እንደሚለው ያንን ጠቢብ ደሃ ሰው ማንም አላሰበውም ነውና ጠቢባን ወድቀዋል፤ ያልተማሩት ነግሠዋል፤ ሀቀኞች ጎስቁለዋል፤ ደላሎች ከብረዋል፤ ስንዴ ከእንድርዳድ፣ዱቄት ከአመድ ተቀላቅለዋል፤ እነዚህ ተለይተው ይታወቁ፤ በአንድ ወንበር አይደባለቁ፤ ሁሉም አቅማቸውን ይወቁ፤ ያልተማሩ ለመማር የተማሩት ለማስተማር ወገባቸውን ይታጠቁ፡፡
ስለዚህ ለሀገራችንና ለሕዝባችን እንዲሁም ለራሳችን ስንል ሰላምን እናስፍን፡፡ በገዳማትና አድባራት ላይ ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ መብላቱ ይቁም፡፡ ውሃውን በጋራ እንጠቀም፡፡ በሥራ አስኪያጆችና በሠራተኞች መሀል ያሉት ደላሎች ይውጡ፤ በደላሎች የተነሣ ብዙዎች ተርበዋል፤ ከሥራ ተፈናቅለዋል፣ ቤተሰብ በትነዋል፡፡ ሁሉም ሰው ጉዳዩን እኩል ያቅርብ፤ሁሉም ልጅ እንጂ ማንም የእንጀራ ልጅ አይሁን፤በቦታው ላይ የተመደብነው ባለሥልጣናት ሰዓታችንን አክብረን ሥራውን ቢሮ ውስጥ እንሥራ ፤ የቢሮ ሥራ በሆቴል አይሠራ፡፡ ባለጉዳይ የሚያቀርበው አቤቱታ ይሣካም አይሣካም በሥርዓት ይስተናገድ፤ ምክንያቱም እኛ ጋር የሚቀርበው ባለ ጉዳይ ሌሊት ማኅሌቱን፤ ሰዓታቱን፤ ኪዳኑን ፤ ቅዳሴውን ጨርሶ በአገልግሎት መከራውን አይቶ የሚመግበንም ጭምር ነውና እናክብረው፡፡
የተከራችሁ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሐላፊዎች እንድትመሩ የተሰጣችሁን ቤተክርስቲያን ከተሐድሶ መናፍቃን ጠብቁ፤ የቀሚስ ውስጥ ምንፍቅና ይቁም፤ የፈራጂያ ሥር ምንፍቅና ከቤተክርስቲያን ይውጣ፤ በአጠቃላይ «መናፍቅ የቤተ ክርስቲያናችንን እንጀራ አይብላ» የቤተ ክርስቲያናችን የቀደመ ክብሯ ይመለስ፣ የክህነት ልዕልና ይመለስ፡፡ በእኛው በአገልጋዮቿ ቅድስት ቤተክረስቲያናችን ክብሯን አጥታለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ክብር የሆነውን ቆቧን፤ ቀሚሷን እና ካባዋን ለብሶ በየመጠጥ ቤቱ እና በየአልባሌ ቦታ መታየት ይቁም፤ የቀደመው የአባቶቻችን ካህናት ሥነ ምግባር ይመለስ፤ በየአብያተ ክርስቲያናት የተመደቡ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች በደጅ ጠኚዎች ብቻ እያሸፈኑ የደመወዝ ቀን ብቻ ብቅ ማለት ይቁም፤ ቤተ ክርስቲያን አክብራ የሾመቻቸው አንዳንድ አስዳዳሪዎች ሥልጣንን መከታ በማድረግ አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያንን መሬት ያለአግባብ መሸጥ እና ማከራየት ይቁም፤ 1 ካሬ 40,000 በሚሸጥባት መዲናችን በ2 ብርና በ7 ብር ብሎም በ20 ብር የቤተ ክርስቲያንን መሬት ማከራየት ይቁም፤ መናፍቃንስ ቢሆኑ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን በደሉ? ምንፍቅናቸውን በኦርቶዶክሳዊት ትምህርት ድል እናደርጋለን፤ ሲያሻንም ከመካከላችንም እንዲወጡ እናወግዛቸዋለን፤ ታዲያ በጉያዋ ውስጥ የተቀመጡትን «የቤተ-ክርስቲያን ያልሆኑ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ማን ያውግዝልን?» እንዲህ ዓይነቱን የመሪዎችን ጭካኔ የሚመለከቱ ምዕመናን ይህቺን ቅድስት ሃይማኖታቸውን ትተው እያዘኑ፤ እያለቀሱ ወደ መናፍቃን ጎራ ይካተታሉ፡፡ ታዲያ በቃለ እግዚአብሔር ሰብከው ከወሰዱብን ይልቅ በመጥፎ ሥነ ምግባራችን እንቅፋት ሆነን ያባረርናቸው ዓለም ይቁጠራቸው፡፡
ስለዚህ በጋራ ሆነን ብልሹ አሠራርን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ፤ከዚህ በፊት በነበረው የአስተዳደር ሁኔታ በግፍ የተበደላችሁ፤ ፍትሕ በማጣት የተሠቃያችሁት እና ልዩ ልዩ የሞራልና ከሥራ የመፈናቀል አደጋ ውስጥ የገባችሁትን ሁሉ በእኔና በመላው የጽ/ቤታችን ሠራተኞች ስም ይቅርታ እየጠየቅኩ የደብር አስተዳዳሪዎችም በግፍ የተባረሩትን አጣርተን ከቅዱስ አባታችን እና ከቅ/ሲኖዶስ አመራር ተቀብለን በምናደርገው የመፍትሔ አቅጣጫ ሁሉ ከጎናችን በመሆን እንድተደግፉን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በዛሬው ዕለት ለተደረገው አቀባበል ዋናው ምክንያቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አምነው የመደቡት ምደባ በመሆኑ ጉባኤው ቅዱስታቸውን እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲያመስግንልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
በመጨረሻም አዲሱ የሥራ አመራር የተሳካና ውጤታማ ሥራ ይሠራ ዘንድ በጋራ ሆነን በአደባባይ የተሰደበችዋን ቤተ ክርስቲያን ከስድቧ እናላቅቃት ዘንድ በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ለአሳራጊዎች መመሪያ እንዲያስተላልፍልን ለእኔና ከእኔ ጋር ለተመደቡ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ወደ ፊት ሊመደቡ ለሚችሉ ሠራተኞች የሦስት ቀን ጸሎት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጃችን እንዲያውጁልን ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለመምህር ይቅርባይ እንዳለ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው የዝግጅት ክፍላችን ይመኝላቸዋል፡፡