“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ”
በዐቢይ ጾም ከሚታሰቡት ሳምንታዊ በዓላት መካከል ከትንሣኤ ክርስቶስ አንድ ሳምንት በፊት በታላቅ ድምቀት የሚከበረው በዓለ ሆሣዕና በመባል ይታወቃል፡፡
በዚህ ዕለት ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በሌሊቱ ስብሐተ እግዚአብሔር በሊቃውንቱ የሚዘመረው መዝሙር ወእንዘሰሙን በዓለ ፋሲካ …” የሚል ሲሆን በጧቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት በቀሳውስቱና በዲያቆናቱ፣ በንባብና በዜማ የሚቀርቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች እንደሚከተለው ተመዝግበዋል፡፡ ዕብ8÷1-ፍ1 ጴጥ1÷13-24 የሐዋ 8÷26-ፍ መዝ 80÷3 ማቴ 21÷1-13 ሲሆኑ በዳዊት መዝሙርና በማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
“ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ÷ በዕምርት ዕለት በዓልነ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ” (መዝ 80÷3) በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፡፡ ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፡፡ መለከት የመዝሙር መዘመሪያ ዕቃ ሲሆን ይኸውም ከአውራ በግ ቀንድ የተሠራ መለከት ነው፡፡ (ዘፀ19÷13) ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በዓላችን እያለ የሚጠቅሰው የዳስ በዓል በመባል የሚታወቀውን በዓል እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በእስራኤል ሕዝብ ሥርዓት የተለያዩ በዓላት የሚከበሩ ሲሆን በዚህ ክፍል የተጠቀሰው በዓል በአስረኛው ቀን የሚከበረውን የስርየት ቀን (ዘሌ16÷29) ተከትሎ የሚመጣ ሲሆን በምድረበዳው ጉዞ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገውን ጥበቃና ክብካቤ (ዘሌ23÷43) የሚአስታውስና ለሚሰበሰበውም መከር የምስጋና በዓል በመሆን የሚአገለግል እንዲሁም በፋሲካና በቂጣ በዓል የተጀመረውንና በየዓመቱም የሚመጣውን የሃይማኖት በዓል ዑደት የሚአጠቃልል ነው፡፡ በበዓሉም በመጀመሪያ ዕለት መለከት በመንፋት ይከበራል፡፡ ከዚህ በላይ የተመለከትነው በዳዊት መዝሙር የተጻፈውን ቃለ እግዚአብሔር ሲሆን በማቴዎስ ወንጌል (21÷1-13) የተጻፈው ቃል እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
“ወደ ኢየሩሳሌም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ ያን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርሷ ጋር ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ ወዲያውም ይሰዳቸዋል፡፡
ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አህያይቱንና ወርንጫዋንም አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፤ ተቀመጠባቸውም፤ ከህዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቄረጡ በመንግድ ላይ ያነጥፉ ነበር፤ የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ፤ ሕዝቡም ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ፡፡
ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው፡፡” (ማቴ21÷1-13)
መሲሕ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚገባ ነቢዩ ዘካርያስ በትንቢት አመልክቶ ነበር (ዘካ 9÷9) ውርንጫይቱ እንደተዘጋጀችለት ኢየሱስ ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም አንዲያመጡለት ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላካቸው ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱን ከነውርንጫዋ አመጠቱለት ÷ ኢየሱስ ግን ከዚያ በፊት ማንም ተቀምጦበት በማያውቀው በውርንጫዋ ነበር የተቀመጠው፤ ደቀ መዛሙርቱ ልብሳቸውን በውሮንጫው ላይ አነጠፉ (ማቴ 21÷7) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ተቀመጡበትና ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ ብዙ ሰዎች ሸማቸውን በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፤ አንድአንዶቹ ሰዎች ከገሊላ ተከትለውታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በኢሩሳሌም የሚኖሩ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡ ለክርስቶስ ተገዢነትታቸውን ለማሳየት ነበር ሸማቸውን መሬት ላይ ያነጠፉት (2ነገ9÷13) ሌሎቹ ደግሞ የደስታና የድል ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ መሬት ላይ አነጠፉ፤ ሕዝቡ “ሆሳዕና” በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ (መዝ 118÷25-26) በሉቃስ ወንጌል 19÷39 መሠረት ከፍተኛ ጩኸትና ጫጫታ ስለነበር በሕዝቡ መካከል ከነበሩት ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን ዝም እንዲያአሰኛቸው ኢየሱስን ጠየቁት፡፡ ኢየሱስ ግን እነርሱ እንኳን ዝም ቢሉ ደንጊያዎች ይጮኻሉ ሲል መለሰላቸው (ሉቃ 19÷40) የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ እንደ መሲሕነቱ በግልፅ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ታላቅ ሁኔታ ደግሞ ዝምታ ሊኖር አይችልም፡፡
የአንድ ምድራዊ ንጉሥ ታላቅ የጦር መሪ ይመስል መሲሕ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በሰንጋ ፈረስ አልነበረም፤ ጻድቅና አዳኝ ትሑትም ሆኖ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ነበር ወደ ኢየሩሳሌም የገባው (ዘካ 9÷9) ለአሕዛብም ሰላምን ለመናገር መጣ፡፡