ሁለት ዓመት ከስድስት ወር የፈጀው አለመግባባት በሰላም ተፈታ

በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሰበካ ጉባኤው መካከል ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በሰላም ተፈታ።
መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል መምሪያ የበላይ ጠባቂ ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል።
የችግሩ ምክንያት በሰንበት ትምህርት ቤቱና በሰበካ ጉባኤው መካከል ሁለገብ ሕንጻን በመገንባት በኩል የሃሳብ ልዩነት በመፈጠሩ እንደሆነ ተብራርቷል።
በአዲስ አበባና በጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መመሪያ ሰጭነት እንዲሁም በሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ በረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዩና በሌሎችም ሽምግልና የተከሰተው አለመግባባት መፍትሔ አግኝቷል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቀኑ የደስታ ቀን መሆኑን የገለጹ ሲሆን መድኃኔዓለም ለእኛ ብሎ የተሰቀለበት፣ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና የተከሰተው ችግር የተፈታበት መሆኑን አብራርተዋል።
ከአሁን በኋላ ስላለፈው ችግር ማውራት አያስፈልግም ይልቁንም ወደፊት ስላለው ልማት ማሰብ ነው የሚያስፈልገው በማለት ገልጸዋል።
አያይዘውም ሥራዎችም በጥንቃቄ እንዲሠሩ፣ አንዱን ከአንዱ በመለያየት ችግር እንዲፈጠር ለሚያደርጉ አካላት ጆሮ መስጠት እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥተው መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት 400 ኩንታል ሲሚንቶ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ ብፁዕነታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተከሰተው ችግር ከልብ ሲያሳስባቸው እንደቆየና አሁን ግን ሰላም በመውረዱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ችግሩ በሰላም መንገድ መፈታቱ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ገልጸው ለሰላም የሚቆሙ ብፁዓን ናቸው በማለት ሰላም እንዲወርድ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለተሻሻለውና ለልማት ለሚውለው ሁለገብ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ ተመርቷል።
ደብሩ የ111 ዓመት ታሪክ ያለው መሆኑን ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ባደረጉት ንግግር በሰላምና በፍቅር የመሠረት ድንጋይ የምንጥልበት ቀን ነው ብለዋል።
የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ሆኑ የሰበካው ጉባኤው አባላት ሃሳባቸው መልካም ሆኖ ሳለ ፍቅር ባለመኖሩ ብቻ ጉዳዩ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ፈጅቷል፤ በዚህም የተጠቀምነው ነገር የለም ይልቁንም ተጎዳን እንጂ ብለዋል።
የችግሩ ምክንያት የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም የደብሩ የሰባካው ጉባኤው አባላትም አይደሉም ሌሎች አካላት ናቸው በማለት ሙሐዘ ጥበባት ገልጸዋል።
በሁለቱ አካላት መካከል የተከሰተው አለመግባባት በእርቅ ይፈታ፣ የተጀመረው ክስ ይቋረጥ፣ በፍቅርና በውይይት ይፈታ፣ ሕንጻው በጋራ ይሠራ ተብሎ በሽምግልና መፍትሔ ላይ እንደተደረሰ አውስተዋል።
ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ ለሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ለረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዩ፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ር ዳዊት ግርማ፣ ለደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ስዩም ወ/ገብርኤልና ለሌሎችም በሽምግልና በኩል አስተዋጽኦ ላደረጉት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዩን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ስዩም ወ/ገብርኤል፣ የደብሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የአከባቢው ምእመናን ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ ፦መ/ር ዋሲሁን ተሾመ