ሀገር አቀፍ ሥልጠና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስር ላሉ አድባራትና ገዳማት የሥራ ኃላፊዎች ቃለ ዓዋዲንና የሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ በጠቅላይ ቤተክህነት ልዑካን ሥልጠና ተሰጠ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከጥር 25_የካቲት 6/2018 ዓ/ም በሁሉም አህጉረ ስብከት ሥልጠናዎች እንዲሰጡ መመሪያ በማውረድና ልኡካን በመመደብ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
ይህንን አስመልክቶም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለያዩ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥልጠናዎች በትናንትናው ዕለት ጥር 29/2018 ዓ/ም ተሰጥቷል።
ሥልጠናው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ስር ላሉ አድባራትና ገዳማት የሥራ ኃላፊዎች በቶታል ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ የተዘጋጀ ሲሆን ቃለ ዓዋዲንና የሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተክህነት በተላኩ ልዑካን ተሰጥቷል።
በሥልጠናው ላይ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ልኡካን ፣ ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ የከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ አእላፍ ፍቅረ ሰላም የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ክፍል ሐላፊ ፣የክፍለ ከተማው የሥራ ሐላፊዎች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው የሥራ ሐላፊዎች ተገኝተዋል።
በሥልጠናው መርሐ ግብር መሠረት “ቃለ ዓዋዲን” አስመልክቶ መጋቤ ሥርዐት ዮሐንስ አሰሙ ከመንበረ ፓትርያርክ ሕግ አገልግሎት መምሪያ እንዲሁም “የሚዲያ አጠቃቀምና መንፈሳዊ ሕይወትን” በሚል ርእስ ደግሞ መምህር ጌታባለው አድማሱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ሥልጠናውን ሰጥተዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው ላይ አስተያያትና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው ሥልጠናው ለቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ መናበብና ትውልዱን ተረድቶ ለማገልገል በእጅጉ እንደሚጠቅም አንስተዋል።
የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ሐላፊ መጋቤ አእላፍ ፍቅረ ሰላም ወረታው በሥልጠናው አስፈላጊነትና ሀገረ ስብከቱ ለሥልጠናው የሰጠው ትኩረት አንስተው ሐሳባቸውን መልእክት አስተላልፈዋል።
ክቡር ሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የመንበረ ፓትርያርክ ባወረደው መመሪያ መሠረት ሥልጠና በሁሉም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እየተካሄደ መሆኑን አስተውሰው ዘመኑን የዋጀ ሥራ ለመሥራት አስፈላጊነቱ የጎላ ነው ብለዋል።
ሥልጠናው ሀገረ ስብከቱ እየሠራቸውና ለመተገበርም በዝግጅት ላይ ላለው ሁሉን አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ተኮር ሥራዎችን ለመሥራት የበለጠ መደላድል የሚፈጥር ነው በማለት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ሥልጠናውን የተሰጡትን የመንበረ ፓትርያርክ ልአካን፣ በሰዓቱ ያዘጋጀው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እንዲሁም ለተሳተፉት የገዳማትና አድባራት የአገልግቶል መሪውችና የሥራ ሐላፊዎች ምስጋናቸውን ገልጸው በተግባራዊነቱ ላይ ሁሉም ለወገኔ_ይጠቅማል ከሚል ሐሳብ ወጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በማስቀደም ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስስበዋል።