የቤተክርስቲያን ታሪክ

ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ

“ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ” “የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ” /መዝ.71,10/

ነቢዩ ዳዊት “ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ወጸላእቱሂ ሐመደ ይቀምሑ፤ ነገሥተ ተርሲስ ወደስያት አምኃ ያበውኡ፤ ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ፤ ወይሰግዱ ሎቱ ኲሎሙ ነገሥተ ምድር ኢትዮጵያውያን በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐመድ ይቅማሉ፤ የጠርሲስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታትም እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል” ብሎ /መዝ.71 9-10/በተናገረው ትንቢት መሠረት ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን የይሁዳ ክፍል በምትሆን በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ጥበበኞች ሰዎች ከምሥራቅ መጡ ” ወደ ቤት ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ጋር አይተው ከፈረስ ከሠረገላ ወርደው ሰገዱለት፤ ሳጥናቸውን ከፍተው ኮረጁዋቸውን ፈትተው ወርቁን ዕጣኑንና ከርቤውን ግብር አገቡለት” /ማቴ.2 1-11/ ብሎ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወልዶ ሳለ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን እንደነበረ ይተረካል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “የግመሎች ብዛት፣ የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ” /ኢሳ.60.6/ ብሎ በትንቢት እንደተናገረው የወርቅ እጅ መንሻ ያቀረበው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እንደነበር ይነገራል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ በትክክል ነው፡፡

ከ1ኛ – 4ኛ ክፍለ ዘመን

“ነዋ ማይ ወመኑ ይከልአኒ ተጠምቆ ” “እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው” /የሐ.ሥ.8፣36/

የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደሆነ መንገድ ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነሆም “ህንደኬ” የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቡዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፤ እርሱም “የተረጐመልኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለው፤ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነብበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፡- እንደ በግ ወደመታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፤ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል” ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ እባክህ ነቢዩ ይህን ስለማን ይናገራል ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ አለው፤ ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡

በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውሀ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?” አለው፡፡ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል” አለው፤ መልሶም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሀ ወረዱ፤ አጠመቀውም፤ ከውሀውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና” /የሐ.ሥ.8፡26-39/ በማለት ወንጌላዊው ሉቃስ እንደተረከው የክርስትና እምነትና ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግሥት በሕንደኬ ጃንደረባ በባኮስ አማካይነት ነው፡፡ ያጠመቀውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወንጌላዊው ፊልጶስ ነው፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” የሚለውን የእምነት ፎርሙላ በመናገር የጀመረና ለዓለም ያበረከተ ኢትዮጵያዊው ባኮስ ነው፡፡

አይሁድና ተንባለት እስከ ዛሬ ድረስ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ” መሆኑን ለማመን አቅቶዋቸው የተቸገሩበትንና ዓለምን የሚያስቸግሩበትን ክህደትና ኑፋቄ ሳይከተል “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውቆና አምኖ በማሳመን ለወገኖቹ ትክክለኛውን እምነት ስለ ሰበከ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምናለች፣ ትሰብካለች፤ ታሳምናለች፡፡ በዘመነ ሐዋርያት የክርስትና እምነትን በመቀበል የመጀመሪያው የወንጌል አዝመራ የሆነው ባኮስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእምነትና ሥርዐተ አምልኮ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ነው፡፡ ለሐዲስ ኪዳን ኢትዮጵያም ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያገኘ የቤተ ክርስቲያናችን መሥራች ነው፡፡ ባኮስ በዚህ ሃይማኖታዊ ጒዞው የሕገ ኦሪትንና የሕገ ወንጌልን ጽድቅ በአንድ ጒዞ በመፈጸም የራሱንና የአገሩን ስም በቅዱስ መጽሐፍ ለማስጠራት በቅቱአል፡፡

ባኮስ ወደ አገሩ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውንና የተረዳውን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን እንደ አስተማረ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊ አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፊልጶስ የክርስትና አባቷ ስለሆነ በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንፃ ጽላት ቀርፃ ታከብረዋለች፡፡ በጸሎቱና በአማላጅነቱም ትታመናለች፤ ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ናትናኤል፣ ቅዱስ በርተሎሜዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ በኑብያና በኢትዮጵያ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን እንደ ሰበኩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች እነሩፊኖስና እነ ሶቅራጥስ መስክረዋል፡፡

በ4ኛው መቶ ዓመት “ቅዱስና ያለ ተንኰል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል” /ዕብ.7፣26/ ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት እንደተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባኛል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፡፡

ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት በ330 ዓ.ም. ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኩዋል፡፡

ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡ በዚሁ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በምልዓት መፈጸም ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ግዛት በሙሉ የወንጌልን ትምህርት ለማዳረስ የሚረዱት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመ፡፡

ይልቁንም በዚያ ጊዜ ሊቀ ካህናት የነበረውን አንበረምን ሕዝበ ቀድስ ብሎ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው በሕዝበ ቀድስም ስብከት የኖባና የሳባ፣ የናግራንና የትግራይ፣ የአማራና የአንጎት፣ የቀጣ፣ የዘበግዱር ሕዝብ በክርስቶስ አምነውና ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስት፣ ከዕብራይስጥና ከፅርዕ ወደ ግዕዝ ቋንቋ መለሰ፡፡ የሳባውያንን የፊደል አቀማመጥ የለወጠውና አዲሱንም ከግራ ወደቀኝ የመጻፍና የማንበብ ዘዴ የፈጠረ እሱ ነው፡፡ ይልቁንም ድምፁን በመከተል 6ቱን የፊደል ድምፆች የጨመረ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል፡፡

ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ሢመተ ጵጵስና ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች፡፡ከዚያም ጊዜ አንሥቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከግብጻውያን ብቻ ጳጳሳት እየተሾሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቈይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያውያን መካከል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጳጳስ፣ አቡነ ፊልጶስ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው እንደተሾሙ ታሪክ ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንታዊት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሥርዐተ እምነት አንድነትና የእህትማማችነት ህብረት ስለነበራት ግብፃውያን ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ብቻ ተወስነው የቀረው የአስተዳደሩና የውስጥ አመራሩ ይዞታ ግን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይካሄድ እንደነበር ታሪክ የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሥርዐተ ትምህርትና በባህል ራሱን የቻለ አቋም የነበራትና ያላት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡