የቅዱሳን ሕይወት(ክብረ ቅዱሳን)
በሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረአማኑኤል
ቅድስና በምንልበት ጊዜ ቅድስናን በሁለት ከፍሎ ማየት ተገቢ ይሆናል፤ ይኸውም፡-
- ሀ. የባሕርይ ቅድስና ፤
- ለ. የጸጋ ቅድስና ማለት ሲሆን የባሕርይ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻ የምንገልጸው ልዩ አገላለጽ ነው፡፡ የጸጋ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ደግሞ ሰማያውያን መላዕክትና ምድራውያን ሰዎች ራሳቸውን ለቅድስና አዘጋጅተው ሲገኙ ቅድስናውን የሚያገኙት የቅድስና ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ልዩ ስጦታ ነው፡፡ በተለይ ምድራውያን ሰዎች በሃይማኖት ጸንተው፤ በበጎ ሥራ ተቃኝተው በቅን ልቡና አግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ቅዱሳን ይሆናሉ፤ ቅዱሳንም ይባላሉ፡፡ ‹‹እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› ተብሏልና፡፡ (ዘሌ 19፡2)
የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን በምንልበትም ጊዜ ብሔራዉያን ቅዱሳንንና ከዉጪ ወደ ኢትዮጽያ መጥተዉ ያበረከቱትን ከፍተኛ መንፈሳዊ አገልግሎት ከግምት ዉስጥ በማስገባት የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅድስናን ሰጥታ፣ በየስማቸዉ ቤተ ክርስቲያን አንፃ፣ ፅላት ቀርጻ፣ ገዳም ገድማ ያከበረቻቸዉና የምታስከብራቸዉ ቅዱሳን በርካታዎች ሲሆኑ በዚህ ፅሁፍ አጠቃሎ መግለጽ ባይቻልም ለግንዛቤ ያህል የአገር ዉስጥና የዉጭ ሀገር ቅዱሳን በማለት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ከፍሎ መግለፅ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለፀዉ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸዉን ፈፅመዉ ዘለዓለማዊ ዕረፍታቸዉን በኢትዮጽያ ምድር በማድረጋቸዉ ብሔረ ሙላዳታቸዉን ለመግለፅ ያህል ታስቦ የተገለፀ ጽሑፍ መሆኑ ከግንዛቤ ዉስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጽያን የሁለት ሺህ ዘመን ቅዱሳን ታሪክ በዚህ ጽሑፍ አምልቶና አስፍቶ መግለፅ ባይቻልም ዝርዝር ታሪኩን ለታሪክ ጸሐፊዎች በመተዉ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አለኝታ የሆኑትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዐበይት መምህራንን፣ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያናችን ስም በየአረፍተ ዘመናቱ መላ ሕይወታቸዉን የሰዉ ዘር የሆነዉን ሁሉ በሥራና በጸሎት በማገልገል፣ እግዚአብሔርን በማመስገን ሕይወታቸዉን መሥዋዕት አድርገዉ ያቀረቡትንና እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነዉን ገድል የፈጸሙትን ሁሉ ቤተክርስቲያናችን የጾታ ልዩነትን ሳታደርግ በገድላቸዉ ጽናትና በትሩፋታቸዉ ብዛት ብፁዕና ብፅዕት፣ ቅዱስና ቅድስት ሊያሰኝ ከሚችል የብፅዕናና ቅድስና ማዕረግ የደረሱ መሆናቸዉን በማረጋገጥና በስማቸዉም ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ፣ ገዳም እንዲገደም፣ ደብር እንዲደበር፣ ገድልና ድርሳን እንዲጻፍላቸዉ፣ ወርሃዊና ዐመታዊ በዓላቸዉ እንዲታሰብና እንዲዘከር በማድረግ በቅዱስነት ያወቀቻቸዉንና ያሳወቀቻቸዉን ኢትዮጰያዉያንና ብሔረሙላዳታቸዉ ከኢትዮጰያ ዉጪ የሆኑትን ቅዱሳንና ቅዱሳትን ስም ዝረዝር በከፊልም ቢሆን እንደሚከተለዉ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡
ኢትዮጰያዉያን ቅዱሳንና ቅዱሳት
1. ሕጽዋ ለሕንደኬ ንግስተ ኢትዮጰያ
የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጰያ የገባዉ ወይም ኢትዮጰያና የክርስትና ሐይማኖት የተዋወቁት ሐዋርያዉ ቅዱስ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት 8፡26-40 ላይ እንደመዘገበው ጃንደረባው እንደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ሥርዓተ አምልኮትን ፈጽሞ በፍኖተ ጋዛ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም. ነው፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያን አባት›› እየተባለ የሚጠራው አውሳብዮስ የወንጌላዊው ሉቃስን ግብረ ሐዋርያት መሠረት አድረጎ ‹‹ሕጽው ለወገኖቹ ሆነ የኢትዮጵያ ሐዋርያ እሱ ነው›› በማለት ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ገጽ 18 ላይ ይመለከቱ፡፡
2. ቅዱሳን ነገስታት አብርሃ ወአጽብሓ
አብርሃ ወአጽብሓ የተሰኙ ቅዱሳን ነገስታት(ወንድማማቾች) እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ፍጹም በሆነ ስምምነት ለ15 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በጋራ ከአስተዳደሩ በኋላ እንደ አበው ሐዋርያት ዕጣ ተጣጥለው አብርሃ በአክሱም፤ አጽብሓ በሸዋ መናገሻ ከተማውን ኤረር በማድረግ መንበረ መንግሥታቸውን ዘርግተው እየተመካከሩ ኢትዮጵያን በማስተዳደራቸው፤ ለሀገሪቱና ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለቱ ወንድማማች ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታቸዋለች፡፡ በስማቸውም ቤተ ክርስቲያን አንጻለች፡፡ ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውንም በየዓመቱ ጥቅምት 4 ቀን እንዲታሰብና እንዲከበርም አድርጋለች፡፡ (ታሪከ ነገሥት አብርሓ ወአጽብሓ ከመምህር ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ 1989 ዓ.ም አዲስ አበባ)
3. አፄ ካሌብ
ከአብርሃና አጽብሓ ቀጥሎ ከተነሡት ቅዱሳን ነገሥታት ክርስትናን በማስፋፋትና በመንከባከብ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደረጉት ከ485-515 ዓ.ም. የነበሩት አፄ ካሌብ ናቸው፡፡
አፄ ካሌብ ስለ ክርስትና መስፋፋት፤ ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ብዙ ተጋድሎን ከተጋደሉና ከአሳለፉ በኋላ መንግሥታአውን ለልጃቸው ለአፄ ገብረ መስቀል አስረክበው፤ መንነው፤ ልብሰ ምንኩስናን ለብሰው ከአክሱም ወደ ሰሜን ምሠራቅ በሚገኘው በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በሚገኘው ዋሻ የምናኔ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ መንግሥታቸውን ለቀው በመነኑበት ሰዓት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነውን ማለትም የነገሡበትን ዘውድ ወደ ጌታ መቃብር ጎልጎታ ልከው በምናኔ 12 ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ በ536 ዓ.ም. ግንቦት 20 ቀን አርፈዋል፡፡ አፄ ካሌብ በምንኩስናና በምናኔ ሕይወት የቅዱሳንን አሠረ ጽድቅ ፈጽመው ያለፉ ደገኛ ንጉሥ ስለነበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቁጥራቸው ከቅዱሳን ነው፡፡ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ 1974 ዓ.ም.)
4. አባ ዮሐኒ
አባ ዮሐኒ ብሔረ ሙላዳችው በክልል ትግራይ፤ በተንቤን ልዩ ስሙ ሀገረ ሰላም ከተባለው ቀበሌ ሲሆን የነበሩበትም ዘመን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በቆላ ተንቤን ደብረ አንሣ(ዓሣ) ከተባለው በረሓ በጾምና በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ከነበሩት ከአባ አሞኒ ጋር እንደ ኖሩ፤ ዕድገታቸውም በእናት ጡት ሳይሆን ቶራ እያጠባች እንዳሳደገቻቸው በገድለ አቡነ ዮሐኒ ተመዝግቧል፡፡ ገዳማቸውም ደብረ አንሣ(ዓሣ) ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውም ህዳር 5 ቀን ይታሰባል፡፡ ( ምንጭ፡- 1. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ 2. Journal of Ethiopian Studies. Vol 3 No. 2 July 1975)
5. ቅድስ ያሬድ
ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ505 ዓ.ም. የተነሣ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዓለም በሚታወቅበት ሙያውና ዕውቀቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ የመንፈሳዊ ዜማ ደራሲ የቅኔ ተመራማሪ፤ ኪሩቤልን በሚያስምስለው ጣዕመ ዝማሬ የተወደደና ድምፅ መልካ ማሕሌትዊ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ድጓ፤ ዝማሬ መዋሥእትና ምዕራፍ የተሰኙ የዜማ መጻሕፍት አሉት፤ የብሉያት የሐዲሳትና የሊቃውንት መጻሕፍት ትርጓሜም ሊቅ ነው፡፡ እነዚህ ከብሉያት ከሐዲሳት ከሊቃውንት መጻሐፍት ለጸሎትና ለማሕሌት የሚስማሙትን ቃላት እየመረጠ ምሥጢራትን ከትርጓሜ እያስማማ ዜማዎቹን በዐራቱ ክፍላተ ዘመን በመፀው፤ በሐጋይ፤ በጸደይና በክረምት በመክፈል የየወቅቱን የተፈጥሮ ሥነ ባሕርይ በአንክሮና በምስጋና በሚገልጽ ጣዕም እንዲዘምሩና እንዲጸልዩ ያደረገ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው፡፡ ዜማውንም ግዕዝ፤ ዕዝል አራራይ በሚል በሦስት የዜማ ስልት ከፍሎ ዘምሮታል፡፡
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን ያዘጋጀው ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ዘመን ነው፡፡ ማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍሎች ለ11 ዓመታት እየተዛዋወረ ሲያስተምር ቤተ ክርስቲያንን ያገለግልና ሲያስገለግል ቆይቷል፡፡
በመጨረሻም በሰሜን ተራራዎች ሥር ካሉት ገዳማት በአንዱ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በጾም፤ በጸሎት፤ በብሕትውና ዘመኑን አሳልፎአል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እስከ ዛሬ እልፈትና ውላጤ ያላገኘው በጣዕመ ዝማሬው በምልክቱ ልዩ የሆነ የዜማ ድርሰቱን ለኢትዮጰያ ቤተ ከርስቲያን ያበረከተ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝክረ ስሙን በጥንቃቄ ጠብቃ፤ በስሙ ጽላት ቀርፃ፤ ቤተ ክርስቲያንን አንጻ፤ ገድሉን ጽፋ በዓለ ዕረፍቱን በየዓመቱ ግንቦት 11 ቀን ታከብራለች፡፡ (ምንጭ፡- The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Faith, order of worship and Ecumenical relations, July 1996)
6. ሌሎች
- ቅዱስ ይምርሃነ ክርሰቶስ
- ቅዱስ ሐርቤ(ገ/ማርያም)
- ቅዱስ ላሊበላ
- ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ
እነዚህ ቅዱሳን የነበሩበት ዘመን ከ11ኛው እስከ 12ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ምስፍንናን ከክህነት፤ ክህነትን ከምንፍስና ጋር አስተባብረው በመያዝ ለክርስትና መስፋፋት፤ ለቤተ ከርስቲያን ዕድገት፤ ለአገር አንድነት የከፈሉት መስዋዕትነት፤ ያቆዩት መንፈሳዊ ቅርስ በዐይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የደም ሥርና የጀርባ አጥንት ሆነው የሚታዩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ ስማቸው ለተጠቀሱው መንፈሳውያን ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፤ ገድላቸውን ጽፋ ለትውልደ ትውልድ አቆይታለች፡፡
(ምንጭ፡- 1. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትና ዛሬ መስከረም 1990 ዓ.ም 2. ዜና መዋዕል ዘብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነሐሴ 1978 ዓ.ም. 3. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብል ሥላሴ 1981 ዓ.ም.)