የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ለሰበታ ጌቴሴማኒ ቤተደናግል ጠባባት ገዳም የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በሰበታ ለሚገኘው እናቶች ገዳም በገዳሙ ውስጥ እየተማሩ ለሚያድጉ ወላጅ አልባ ህፃናት እና ገዳማዊያን የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የማዕድ ቤት ቁሳቁስ ፤የምግብና መጠጥ ማቅረቢያ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ድጋፍ አድርጓል ።
ድጋፉን ለገዳማዊያን እናቶች ያስረከቡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለገዳሙ የቀረበው ድጋፍ ከገዳማዊያኑ መልከ ብዙ ሥራ አኳያ ጥቂት መሆኑን ገልፀው ኮሚሽኑ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ድጋፉን መስጠቱን ገልጸዋል ።
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሰበታ ለሚገኘው ጌቴሴማኒ ቤተደናግል ጠባባት ገዳም “በቀጣይ ሰፋ ያለ ነገር ይዘን እንመለሳለን” ሲሉም በዚሁ ጊዜ ቃል ገብተዋል።
ብፁዕነታቸው ገዳሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብቸኝነት ሕፃናትና ሴቶች ተለይተው የሚያድጉበትና የሚማሩበት ፤ መንፈሳዊ ሕይወታቸውንም ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማጋመድ ራሳቸውን የሚያንጹበት መሆኑን በመጠቆም የእናቶች ገዳሙ የሁሉንም ወገን ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል።
የጌቴሴማኒ ቤተደናግል ጠባባት ገዳም እናቶች በበኩላቸው በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ለተደረገላቸው ዓመታትን የተሻገረ ድጋፍ አመስግነዋል።
ዕርዳታው በገዳሙ የሚገኙ ወላጅ አልባ ልጆችን ተስፋቸው የሚያለመልም ከመሆኑ ባሻገር ገዳማዊያን እናቶችንም ደስ በማሰኘት ለአገልግሎት የሚያፋጥን ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ሰበታ በሚገኘው የገዳሙ ግቢ ውስጥ የቁሳቁስ ድጋፉን ርክክብ ሲያካሂድ የገዳሙ ሕፃናት እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግነዋል።
የጌቴሴማኒ ቤተደናግል ጠባባት ገዳም ሰበታ በሚገኘው ገዳም 215 ፤ ድሬዳዋ ባለው ቅርንጫፉ ደግሞ 120 ወላጅ አልባ ሕፃናት እያስተማረ የሚያሳድግ ታላቅ የበረከት ስፍራ ነው።
©eotc tv