ኦሮቶዶክሳዊ ዜማዎችና መዝሙሮች
ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እና አጼ ገብረመስቀል
የዜማ አጀማመር
በንቡረ ዕድ ኤልያስ አብረሃ
ዜማ ማለት ጣዕም፣ ለዛና ስልት ባለው ተከታታይ ቅንቀና የሚያሰሙት ድምፅ ማለት ነው፤ ወይም በልዩ ልዩ ሥነ ድምፅ ተቀነባብሮ፣ ተደራጅቶና ተስማምቶ ልዩ ስሜትና ተመስጦ ሊሰጥ በሚችል መልኩ የሚያሰሙት ቅንቀና ነው፡፡ ዜማ የተጀመረው በጥንተ ፍጥረት በመላእክት አንደበት ነው፤ መላእክት እንደተፈጠሩ ወዲያውኑ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን በጣዕመ ዜማ አመስግነዋል ኢዮ.38፣6፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔር ሰውንና መላእክትን መፍጠሩ ስሙን አመስግነው ክብሩን እንዲወርሱ ነውና በጣዕመ ዜማ ማመስገንን በባሕርያቸው ውስጥ እንደ አንድ መሠረታዊ ፍላጎት አድርጎ ፈጥሮላቸዋል፤ ከዚህም የተነሣ ዜማን የመውደድ ዝንባሌ ተፈጥሮአዊ ሆኖ ይገኛል፤ ዜማን የመውደድ ዝንባሌ በመላእክትና በሰዎች ይበልጥ ጐልቶ ይታይ እንጂ ሕይወት ባላቸው በሌሎች ፍጡራንም በብዛት የሚታይ ነው፤ ለምሳሌ “አዕዋፍ ዘሠናይ ዜማሆሙ” ተብሎ የተመሰከረለትን የአዕዋፍ ዜማ መጥቀስ ይቻላል፤ እንግዲህ ይህንን ሁሉ ስንመለከት የስጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ፍጡራንን በባሕርያቸው በዜማ የማመስገን ፍላጎትና ዝንባሌ እንዲኖራቸው አድርጎ በመፍጠሩ የዜማ መገኛውና ምንጩ እርሱ ራሱ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ በጣዕመ ዜማ ማመስገን በሰማያውያን ፍጡራን ዘንድ የማያቋርጥ መደበኛ ሥራ ነው፤ ራእ.4፣9፣ ኢሳ.6፣2-4፡፡
እንደዚሁም ዜማ በተፈጥሮ የተገኘ ተወዳጅ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን ሁሌም የመንፈስ ምግብ ነውና ሰዎች ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ ሲጠቀሙበት ኖሮዋል፤ ዘፍ.4፣21፤ ከዚህም የተነሣ ጣዕሙ፣ ይዘቱና ስልቱ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንሥቶ ከጣዕመ ዜማ የተለዩበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኝ ሕዝብ የራሱ የሆነ ዜማ አለው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ዜማ በአምስት ዓይነት ተከፍሎ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፤ እነዚህም፡-
- እግዚአብሔር የሚመሰገንበት መንፈሳዊ ዜማ /ማህሌት/
- ሕዝብ በደስታ ጊዜ የሚጠቀምበት የደስታ ዜማ /ዘፈን/
- ሕዝብ በኀዘን ጊዜ የሚጠቀምበት የኀዘን ዜማ /ልቅሶ/
- ነዳያን በችግር ጊዜ የሚለምኑበት የልመና ዜማ /ልመና/
- በሰልፍ ጊዜ ለመቀስቀሻ የሚጠቀሙበት የፉከራ ዜማ /ቀረርቶ/ ናቸው፡፡
ዜማ ለእነዚህ ሁሉ የጋራ መጠርያቸው ነው፤ ሆኖም የዜማዎቹ ድምፀ ቃና፣ ሥነ ቃልና እንቅስቃሴ የአንዱ ከሌላው የተለያዩ ናቸው፡፡ እንግዲህ ስለ ዜማ አጀማመርና አመጣጥ በአጭሩ ይህን ያህል ካልን በኋላ የዚህ ጽሑፍ ዋና ርእስ ወደሆነው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ጸዋትወ ዜማ” ወደሚለው ዝርዝር ገለጻ እንገባለን፡፡
1. ቅድመ ክርስትና የነበረ ዜማ
በሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ
የኢትዮጵያ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ከአምልኮተ እግዚአብሔር የተለዩበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም ዜማ ተፈጥሮአዊ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን በተፈጥሮ ያገኙትና የራሳቸው የሆነ የእግዚአብሔር ማመስገኛ ጣዕመ ዜማ አልነበራቸውም ማለት አይቻልም፡፡
ኦሪት ገና ወደኢትየጵያ ከመግባቱ በፊት ስብሐተ እግዚአብሔር፣ አምልኮተ እግዚአብሔርና ፈሪሀሃ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እንደነበረ ይታወቃል፤ አምልኮት ካለ ምስጋና አለ፤ ምስጋናም ካለ ዜማም አብሮ አለ፤ ከዚህ ሁኔታ ስንመለከት ከሕገ ኦሪት መምጣት በፊት በኢትዮጵያ በዜማ ማመስገን ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም በኋላ በኢትዮጵያ ዘመነ አበው አልፎ ዘመነ ኦሪት ሲተካና በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ታቦተ ጽዮንና ሌዋውያን ሲመጡ የመዝሙራት መጻሕፍት አብረው ስለመጡ የዜማው መልክ በመሣርያ፣ በዓይነትና በአጠቃቀም ተጨማሪ መልክ መያዙ አልቀረም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ /መዝ.150፣1-5፣ ዜና መዋ.ቀዳ.15፣16፤ 16፣4-37/ እንደሚያስረዳው በዳዊትና በሰሎሞን ጊዜ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ፣ በበገና፣ በዕንዚራ፣ በቀንደ መለከት፣ በዕልልታና በሆታ እግዚአብሔር በዜማ ይመሰገን እንደነበረ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ ምስጋናና የምስጋና መሣርያ በዋነኛነት ይጠቀሙ የነበሩ የታቦተ ጽዮን አገልጋዮች የነበሩ ሌዋውያን ካህናት መሆናቸውንም መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል /ዕዝ.3፡10/፡፡
በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ሌዋውያንም አብረው ስለመጡ ዜማቸው፤ ማሌታቸውና የማሌት መሣርያቸው ሁሉ በዚያን ጊዜ አብሮ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶአል፤ አገሪቱም ይህንን የዜማ ስልት ከነመሣርያው እስከ ዘመነ ክርስትና ስትገለገልበት ቈይታለች፤ የዚህ ዓይነቱ ጣዕመ ዜማ አገልጋዮችም ታቦተ ጽዮን በምትኖርበት ድንኳን ውስጥ ከዓመት እስከ ዓመት ያለማቋረጥ የሚያገለግሉ ስለነበሩ “ካህናተ ደብተራ” ይባላሉ፤ ትርጓሜውም ታቦተ ጽዮን በምትኖርበት ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ማለት ነው፤ ይህ ስም ከጥንት ጀምሮ የቈየ የመዓርግ ወይም የሙያ ስም ነው፤ ስያሜው እስከ ቅርብ ጊዜ ትልቅ የመዓርግ ስም ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይሰጥ ስለነበረ ሊቃውንቱ ደብተራ እገሌ እየተባሉ ይጠሩበት ነበር፡፡
እነዚህ በዘመነ ኦሪት የመጡ የዜማ መሣርያዎች፣ አለባበሶችና የመዝሙር አጠቃቀም ስልቶች እስከዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገልባቸው ትገኛለች፡፡
ለምሳሌ ከዜማ መሣርያዎች መካከል፡- ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መለከት፣ መሰንቆ፣ በገና ወዘተ ይገኙበታል መዝ.150፣1-5፤ ከአለባበስም ረጅም ቀሚስ፣ ጥምጥም፣ መጐናጸፊያ /ጋቢ/ እና ካባ ወዘተ ይገኙባቸዋል ዘሌ.8፣7-9 ፡፡
ከመዝሙር ስልት ደግሞ የቅዱስ ያሬድ የምዕራፍ ዜማ ምዕዛል ስልት ይገኝበታል ዕዝ.3፣11፡፡
2. ዜማ በክርስትና ምሥረታ ጊዜ፡-
ኢትዮጵያ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመርያ አካባቢ የክርስትና ሃይማኖትን በብሔራዊ ደረጃ ስትቀበል ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማስፈጸምያ የሚሆን ክርስቲያናዊ ዜማ ነበራት፤ ይህ ዜማ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚታየው ለአገልግሎት ማስፈጸሚያ ያህል በመጠኑ ያገለግል የነበረ ዜማ እንጂ እንደ አሁኑ ጥልቀት፣ ምጥቀትና ርቀት ያለው፣ የተደራጀና የተቀነባበረ ዜማ አልነበረም፤ ከ330 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አምስት መቶ ዐርባ ዓ.ም. በዚሁ ዜማ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሲሰጡ፣ እግዚአብሔርም ሲመሰገን ኖሮአል፤ ከአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን እግዚአብሔር ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሰዎች በፊቱ ይሰግዳሉ /መዝ.71፣9/ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች /መዝ.67፣31/ ሲል በዳዊት አንደበት የመሰከረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትና አምልኮተ እግዚአብሔር በልዩ ጣዕመ ዜማ እንዲታጀብ በመፈለጉ ከአኲስም ጽዮን ካህናተ ደብተራ መካከል አንዱን ካህን ለታላቅ ሰማያዊ ጣዕመ ዜማ መገለጥ መረጠ “ቅዱስ ያሬድ”፡፡