ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ ቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አቅንተዋል
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ወደ ቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አቅንተዋል።
ከቅስነታቸው ጋር ፲ ልዑካን ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል ለማክበር ፣በበዓሉ ላይ የሚገኙ ምዕመናንን ለማስተማር፣ቃለ በምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ለመስጠት ዛሬ ማለዳ ወደ ድሬዳዋ ተጉዘዋል።
ልኡኩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን፣የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅንና መምሪያ ኃላፊዎችን የሚያካትት ነው።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች፣ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለቅዱስነታቸውና ለልዑካን ቡድኑ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።
ቅዱስ ፓትርያርኩ እና የልዑካን ቡድኑ ድሬዳዋ አውሮፕላን
ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዕ አቡነ በርተሎሚዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በአቶ ከድር ጁዋርና በካቢኔ አባለቱ፣ በሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ በካህናትና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የክብር አቀባበል ይደረግላቸዋልም ተብሏል።
በድሬዳዋ ቆይታቸውም በድሬዳዋ ገብረ መንክራት ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን የተሰራው ሁለገብ ሕንጻ ይመርቃሉ፣በድሬዳዋ መልካ ጀብዱ ጌቴሴማኒ ጠባባት ገዳም ሕጻናት ማሳደጊያ በመገኘትም ታዳጊዎችን በመጎብኘት ትምህርተ ወንጌል፣ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጡ ይሆናል።
©የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ