ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር ትውውቅ በማድረግ የሥራ መመሪያ ሰጡ!
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ አእላፍ በላይ ፀጋዬ ጋር በመሆን ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር ትውውቅ በማድረግ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ እኛ መልእክተኞች ነን፣ ከላይ ተልከን ቤተ ክርስቲያንን እንድናገለግል መጥተናል ስለዚህ በሀገረ ስብከቱ የነበረው መልካም ገጽታ በማስቀጠል ስህተቱን ደግሞ በማረም እንሠራለን ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ ትልቅና በሀገሪቱ መዲና የሚገኝ ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ ግን በመልካም ስም እንደማይነሳ ገልጸዋል።
አያይዘውም ሀገረ ስብከቱ ለምን ታመመ ሲሉ በመጠየቅ መድኃኒት እንደሚያስፈልገው ጠቅሰው አሁን መልካም ስም እንዲኖረው በጋራ ሆነን ፈውስ እናበጅለት ዘንድ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሀገረ ስብከቱ ተሻጋሪ ራዕይ ሊኖረው ይገባል፣ራሱን ችሎ የስብከተ ወንጌልመርሐግብር እንደ አድባራቱና ገዳማቱ ማዘጋጀች አለበት በማለት አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገረ ስብከቱ ከፐርሰንት ውጪ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ እና መንበረ ጵጵስና እንዲኖረው እንሠራለን ሲሉም ገልጸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ አእላፍ በላይ ፀጋዬ በሀገረ ስብከቱም ሆነ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ብልሹ አሠራር የሚፈጠረው ኃላፊነታችን ሳንወጣ ስንቀር መሆኑን በመግለጽ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የብፁዕ አባታችን መመሪያ ተቀብለን የሀገረ ስብከቱ መልካም ገጽታ ለመገንባት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተደግፈን የአቅማችን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም ሐሳብ የተሰጠ ሲሆን ብፁዕነታቸው ካዳመጡ በኋላ የተሰጡትን አስተያየቶች አድንቀው ሥራቸውን ለመሥራት እንደግብአት እንደሚጠቅማቸው ገልጸዋል።
ሀገረ ስብከቱ ለአንዱ የቤት ልጅ ለአንዱ የእንጀራ ልጅ እንደማይሆን በመግለጽ ሥራቸውን ጥናት በማካሄድ እንደሚጀምሩና በየጊዜው ከሠራተኞች ጋር ግምገማና ውይይት እንደሚኖር ተናግረዋል።
በመጨረሻም በፁዕነታቸው አሁን ላገለግል መጥቻለሁ የሀገረ ስብከቱ መልካም ስም ይመለስ ዘንድ አብረን እናገለግላለን፣ እኔ ተመሳስዬና አስመስሎ መሥራት አልፈልግም ሲሉ ገልጸዋል።
የአቅሜን ያህል ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም በእውነትና በትክክል እሠራለሁ እናንተም ልጆቼ ልትመስሉኝና ልትከተሉኝ ይገባል ሲሉ አባታዊ መመሪያና መልእክት አስተላልፈዋል።