ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ምሥጢር ማለት ቃሉ የግሪክ ቋንቋ ሆኖ ቃሉ ከግዕዝና ከአማርኛ በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ድብቅ ፣ ስውር፣ ሽሽግ፣ ረቂቅ ፣ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን ይኸውም የፍጡር ሚሥጢርና የፈጣሪ ሚስጥር በመባል ይታወቃል፡፡ የፍጡር ምስጢር ሁለት ይዘት አለው፡፡ የሰውና የመላዕክት ምስጢር ይባላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ የእግዚአብሔር ሚስጥር ይህ የከበረ የተወደደ የሚናፈቅ የበረከት ስጦታ ነው፡፡ ብርሃነ አለም ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በከበረ ቃሉ ገልፆታል፡፡ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ /በክርስቶስ/ አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱን የነብሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይናገርና ክብር በሞላበት ሀሴት ደስ ይበላችሁ”፡፡ በማለት ስውር ረቂቅ ከሆነው ጸጋ እግዚአብሔር የምንሰጠው ሀብት መሆኑን በማብራራት ገልፆታል፡፡ በዚህ መሰረት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከሚፈጸሙት ሚስጥራት በቁጥር 7 ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ውሳኔነታቸው ለሰባቱ ሰማያት ስብዐተ እግዚአብሔር ለማይከፈልባቸው ከተሞች ገላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት ሚስጥራት ቤተክርስቲያን የሚስጥርነታቸው ምክንያት በአይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚህ ሚስጥራት አማካኝነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምስጢር ይባላል ብለው ስውርነቱን ረቂቅነቱን ይናገራሉ፡፡ ሰባቱ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን የሚባሉት እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፡፡
- ጥምቀት
- ሜሮን
- ቁርባን
- ክህነት
- ንስሀ
- ቀንዲል
- ተክሊል ናቸው፡፡
1. ሚስጢረ ጥምቀት
ይህ ምሥጢረ ጥምቀት ከኃጢያት ነፃ የምንሆንበት ከዲያቢሎስ አገዛዝ አርነት የምንወጣበት ከእግዚአብሔር በጸጋ የምንወለድበት የምስጢር አይነት ነው፡፡ በቅሰዱሳት መጻህፍት እንደተገለጸው በነብየ እግዚአብሔር በቅዱስ ሕዝቅሌል ት.ሕዝ 36፡25 “ጥሩ ውሀንም ጥምቀትን እረጫችኋለሁ፡ እናንትም ትጠራላችሁ ከርኩስነታችሁም ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስ ልብ እሰጣችኋለው” በማለት የዚህን ምስጢር ክብርነት በረከትነት አምልቶ አስፍቶ ተናገሯል፡፡ በዚህ ሀሳብ ሌሎች ንፁሐን አበው ሀዋርያት ተባብረውታል፡፡ በምልአት ሰብከውታል፡፡ የሐዋ.2፡38 ፣ 1ቆሮ 6፡11 ፣ ዮሐ. 3፡5 ፣ ኤፌ 5፡26 ፣ ገላ 3፡27 ፣ ቲቶ 3፡5 ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት ምስጢር ነው፡፡ ከመጸሕፍ ቅዱስ ውስጥ ጥምቀት ብዙ ምሳሌዎች ይኖሩታል፡፡ እነሆ ከማየአይኅ የዳነበትን መርከብ ቅዱስ ጴጥሮስ የጥምቀት ምሳሌ እንደሆነ ገልጾታል፡፡ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ምዕመናን ከሐጢያት ከጥፋት የሚድኑት በጥምቀት ነውና
ቅዱስ ጳውሎስም እስራኤል ከግብጽ የባርነት ቀንበር ተላቀው የኤርትራን ባህር ተሻግረው ወደምድረ ርስት ያደረጉትን ጉዞ የጥምቀትን ምሳሌ አድርጎ አመስጥሮታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 10፡1-2 ምዕመናን ባህረ ኃጢያትን ተሻግረው ምድረ ርስተ መንግስተ ሰማያትን የሚወርሱት በጥምቀት ነውና፡፡ ዳግመኛም ይህ ብርሃናዊ ሐዋርያ ጥምቀትን በሞትና በመቃብር ይመስለዋል፡፡ ሮሜ 6፡3-4 ቆላ 2፡12 በሞት ጊዜ ነፍስና ስጋ እንደሚለያዩ በጥምቀትም አሮጌው ሰውነት ይሞታል ይቀበራል አዲስ ሰውነት አዲስ ሕልውናን ይጀምራልና፡፡
2. ምስጢረ ሜሮን
ይህ ቃል የጽርዕ ቋንቋ ነው ትርጉሙም መአዛ ያለው የሚያውድ ፣ የሚጣፍጥ፣ ልብ የሚመስጥ ፣ ጣዕም ያለው መልኩ ጽርየቱ ዘይት ነው፡፡ በግዕዝ ቅብዕ፣ ቅብዐ ሜሮን ይባላል፡፡ ከብዙ እጽዋት ተቀምሞ የሚሰራ ነው፡፡ ሕዝበ እስራኤልን የሚያስተዳድሩ የእግዚያብሔር እንደራሴዎች ነገስታትን መሲሀን የሚባሉት ለዚህ ቅብ ተቀብተው ስለሚነግሱ ነው፡፡ ዘፍ 20፡23 1ኛ ሳሙ 10፡1 ዘዳ 28፡41 1ኛ ሳሙ 9፡6 1ኛ ነገስት 1፡34 ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው የቤተመቅደስ ነዋያተ ቅድሳትን አስቀድሞ በዚህ መታተም አለባቸው፡፡ ከተቀቡ በኋላ ለቤተ መቅደስ እንጂ ለተራ አገልግሎት አይውሉም ስለ ቅብዐ ሜሮን ቅዱስ መጽሐፍን የፃፉ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ቅብዐት ይሉታል፡፡ 2ኛ ቆሮ 1፡21 ዮሐ 2፡20 ቅብዕን በመንፈስ ቅዱስ ማህተምን ይሉታል፡፡ ኤፊ 1፡13 ፣4፡30 ይህ ቅብዓ ማህተመ ሕይወት በመሆኑ ለአገልግሎት ይውላል፡፡
3. ምሥጢረ ቁረባን
ይህ ቃል የሱርስት ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም አምኃ ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሥጋውና ደሙ የተሰጠን በነፃ ያለ ዋጋ ሳይገባን በችሮታ ነውና፡፡ በቤተክርስቲያን ምሥጢራት ሁሉ መደምደሚ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ መስዋዕት ማቅረብ የተጀመረው በአዳም ጊዜ ሲሆን ከአዳም እስከ ሙሴ የተነሱ አበው ሁሉ በህገ ልቦና ለእግዚአብሔር መስዋት ይሰው ቁርባን ያቀርቡ ነበር፡፡ መስዋዕታቸው ከእንሰሳ ቁርባናቸው ከእህልና ከአትክልት ማለት ከስንዴ እህል፣ ከወይን ፍሬ የሚቀርብ ነው፡፡ ዘመነ ኦሪት በብሉይ ኪዳን በሙክራብ የተሰዋ እንሰሳት ሁሉ በአዲስ ኪዳን በቤተክርስቲያን ለሚሰዋው ሁሉ የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ ያበረከተው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት ለአምላክ የሥጋውና የደሙ ምሳ ሆነው አልፈዋል፡፡ ከምሥጢራት አንዱ መሆኑ ሕብስቱ ተለውጦ የክርስቶስ ሥጋ ጽዋው ተለውጦ የክርስቶስ ደም ሲሆን አይታይም፡፡ ነገር ግን እምነት ያለው ሁሉ በእምነት መነጽር ይመለከተዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሳይታይ የሚወደድን ሕይወት ለማግኘት ከቁርባን በፊት ንስሐ መግባት ለአስራ ስምንት ሰዓት መጾም አለበት፡፡ ንጽሕናውን በጠበቅ አለበት፡፡ መምክረ ካህን ጸንቶ መገኘት ያስፈልጋል፡፡
4. ምሥጢረ ክህነት
ይህ ቋንቋ የግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ተክህነ አገልገለ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ክህነት የተጀመረው በአባታች አዳም ነው፡፡ ክህነት የአገልግሎት ስም ሆኖ የቤተክርስቲያን ከፍተኛ መንፈሳዊ ማዕረግ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በልጅነት አክብሮ ነብይና ካህን አድርጎ ሾሞ በኦሪት በወንጌል ሥርዓት እስኪወሰን ድረስ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ የነበሩ አበው በበረከት አበው ከእግዚአብሔር እየተሾሙ ትንቢትን ክህነት ከቅዱሱ መንፈስ እየተቀበሉ (እየተሾሙ) በነብይነታቸው ያለውን የሚመጣውን ሲገልጽ ሲያስተምሩ በሀብተ ክህነታቸው መስዋዕት ሲቀርቡ ነበር፡፡ ክህነት በዘመነ ኦሪት ለሌዊ ነገድ ከተሰጠ በኋላ ሲወርድ ሲወራረድ እስከ ክርስቶስ ደርሷል፡፡ ታላቁ ሊቀ ካህናት እየሱስ ክርስቶስ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕት እንሰሳ ሳሆን እራሱን መስዋዕት፣ እርሱ ሰዋዒ ሆኖ ወደ መቅደስ ገብቷል፡፡ ዮሐ 20፡22 ማሬ 18፡18 1ኘና ቆሮ 4፡1 ማሬ 28፡20
5. ምሥጢረ ንስሐ
ይህ ቃል የግዕዝ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም በሰሩት ኃጢያት መጸጸት ምነው ባልሰራሁት ባላደረኩት ብሎ ማልቀስ ወደ ኃጢያት ላለመመለስ መወሰን፣ በሕጉ ጸንቶ ለመኖር ቃል መግባት፡፡ ክርስቲያን በጥምቀት ከአለም ክፉ ስራዎች ሁሉ የተለየ ነው፡፡ ህይወቱ ለክርስቶስ የተሰጠ ነው፡፡ ሮሜ 12፡1 የመጨረሻው ግቡና ዓላማው ሥርየተ ኃጢያትን ማግኘት እና የዘላለም ሕይወት መወረስ ነው፡፡ አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 1ቆሮ 6-19
6. ምሥጢረ ቀንዲል
ይህ ቃል የላቲን ቋንቋ ነው ትርጉሙም ፍፁም መብራት ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ሚስራት አንዱ ቀንዲል ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘይት የፈውስ ምልክት ነው፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚሰቃዩ ህሙማን ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ቁስለኞች እየተቀቡ ይፈወሱ ነበር፡፡ ኢሳ 1፡6 ሉቃ 10፡34 ራዕ 3፡18 ማር 6፡13 ይህ ቅብዓተ በሐዲስ ኪዳን ለሚጠመቁ ከሚደረግ ቅብዐ ሜሮን ጋር ግንኙነት የለውም ራሱን የቻለ ሕሙማነ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ሕሙማነ ነፍስ ኃጥአን የሚቀቡት ፈውስ የሚያገኙበት ነው፡፡ ማር 6፡13 ያዕ 5፡13-15 ራዕ 1፡17፡፡
7. ምሥጢረ ተክሊል
ይህ ማለት “ተከለለ” ተቀናጀ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ በሥርዓተ ጋብቻ ቅደም ተከተል መሰረት በመተጫጨት እና በቃል ኪዳን የተመሰረተ ጋብቻ በተክሊል ይፈጸማል፡፡ ቤተክርስቲያን ምስክርነት የሚፈጸመው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰጥ ስለሆነ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በተክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በትክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡ ዘፍ 1፡27-28 ፣ 2-18 ማቴ 19-4 እነዚህን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አውቀን ተረድተን የእምነታችን ፍጻሜ የሆነውን አምላካችንን ለተፈጠርንለት ዓላማ በመገዛት የነፍሳችንን መዳን ልናረጋግጥ ይገባል፡፡
ለዚህም ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር እንዲረዳን የወላዲተ አማላክ አማላጅነት እንዳይለየን የጻድቃን ፀሎት የቅዱሳን በረከት እንዳይለየን ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!!