ሰበካ ጉባኤ እና ዓላማው
ሰበካ ጉባኤ፡- በተለይ ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘመናዊ መዋቅር ያላት ሆና እንድትተዳደር በተደነገገው ህግ ቃለ ዓዋዲ መመስረት ጋር አብሮ የተጀመረ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው፡፡
ሰበካ ጉባኤ በቃለ አዋዲ አንቀፅ 5 መሰረት የሚከተሉት አለማዎች አሉት፡፡
- ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ፤
- የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች ሐዋርያዊ ተግባር ለማደራጀትና እንደዚሁም ችሎታቸውንና ኑሮአቸውን ለማሻሻል፤
- ምዕመናንን ለማብዛት እንደዚሁም በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ ፤
- የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማሻሻልና በማናቸውም ጉዳይ ራሷን ለማስቻል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቃለ ዓወዲው አንቀጽ 6 ላይ ሰበካ ጉባኤው የሚከተሉትን ተግባራት እንደሚያከናውን ተደንግጎ ይገኛል፡፡
- የእግዚአብሔርን ወንጌል መንግስት ለመስበክና ትምህርቱንም ለማስፋፋት፤
- መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርት ቤትን ለማቋቋምና ለማደራጅት፤
- መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎትን ለምዕመናን ሁሉ ለማደረስ፤
- ሰንበት ትምህርት ቤትን ለማቋቋምና ለማጠናክር ፤
- የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ለምዕመናን ሁሉ ለማድረስ፤
- ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚያስፈልጉትን ሁሉ ለማሟላት፤
- የቤተክርስቲያን አስተዳደርና አገልግሎት በቅዱሳት መጻህፍት መሰረት በህግና በሥነ-ሥርዓት ለመምራት፤
- ቤተ ክርስቲያንን በሀብትና በንብረት በኩል ራሷን ለማስቻል፤
- የቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት እዳይባክን፣ እየተመዘገበ እንዲጠበቅ፣ እንዲለማና እንዲያድግ ለማድረግ፣
- ህገ ቤተክርስቲያን በሚፈቅደው መሰረት ከበላይ የሚሰጡትን ህግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪዎች፣ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች ለመፍጸምና ለማስፈጸም፤
- በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚገኙ ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያት በማናቸውም ጉዳይ እርስ በእርሳቸው ተባብረውና ተረዳድተው እንዲሰሩ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ፣
- ልዩ ልዩ የምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን ለማቋቋምና አገልግሎታቸውን ለማሟላት፣
- የህንፃ ሥራ፣ እድሳት፣ ጥገናና የመሳሰሉት ሥራዎች ሁሉ ወቅቱን ጠብቀው የሚፈጸሙበት እቅድና መርሃ ግብር ማዘጋጀት በተግባር መዋላቸውንም ለመቆጣጠር፣
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮችን ብዛት ፣የሰበካውን ገንዘብና ንብረት ገቢና ወጪ የመሳሰሉትንም እስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በወቅቱ እየመዘገቡ በሪፖርት እንዲገለጽ ለማድረግ፤
- በዚህ ቃለ ዓዋዲ መሰረት ማናቸውንም ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ጉዳይ ለመፈጸምና ለማስፈጸም፤
- በዚህ አንቀጽ ከንዑስ አንቀጽ 4 እስከ 14 የተዘረዘሩትን ተግባሮች በቅድሚያ እያጠና ተገቢውን ለማድረግና አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ ለማስፈጸም፡፡