ምግባረ ሰናይ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት

‘’ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።’’ ያዕ. 1፡17

አረጋውያን በዕድሜ ሳቢያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማቃለል ማህበራዊ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በዓለማችን፣ በሀገራችን ብሎም በመዲናችን አዲስ አበባ በፈጣን ሁኔታ እያደገ የመጣው የአረጋውያን ብዛት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፉ ቀውስ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። አረጋዊነት በሕዝብ ጤና ዘርፍ የሚመዘገብ ውጤት ነው፡፡ አረጋውያን ለኅብረተሰብ የሚጠቅም ዕውቀትና ችሎታቸውን በመጠቀም ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ መርዳት ይጠበቅብናል።

በሰው ልጆች አኗኗር ውስጥ ያለው የመተሳሳብ የመረዳዳትና እና የመከባበር ባህል ከክርስቶስ የማያልቅ ፍቅር የመነጨ መሆኑ  ለሁላቸችን ግልጽ ነው፡፡  ፍቅር ሁሉ ነገር  ነውና ለደከሙት ብርታት፣ ለታመሙ ፈውስን፣ ተስፋ ላጡት ተስፋን ይሠጣል፡፡ ይሁንና ይህን ክርስቲያናዊ ፍቅር  ማግኘት ከሚገባቸው ማህበረሰብ ወጥተው ጎዳና የወጡ፣ የሰው እጅ የሚጠብቁ በርካታ አረጋውያንን ማየት የተለመደ  አጋጣሚ እየሆነ መጥቶአል፡፡

እነዚህ አረጋውያን እናቶችና አባቶች በህይወት ዘመናቸው የሚችሉትን ሁሉ አቅምና ጉልበታቸው ባልደከሙበት ወቅት በየተሰማሩበት የሥራ መስክና ሞያ ለሀገራቸውና ለወገናቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ዛሬ ግን አብዛኛዎቹ አረጋውያን ያለ ጠዋሪና ደጋፊ በየጎዳናውና በየእምነት ቤቱ ደጃፍ ወድቀው ይገኛሉ።

በዚህ ሰብአዊ መብት እንዲከበር የሰው ልጆች ሁለንተናዊ ደህንነት እንዲጠበቅ እየተሰበከ ባለበት ዘመን  በየአጥቢያ አብያተክርስቲያናት በር ተኮልኩልው ያሉ አረጋውያንን እና አረጋውያት ቁጥራቸው ብዙ ከመሆኑም ባሻገር መጠነ ሰፊ ችግር ላይ የወደቁ ናቸው፡፡ ከችግሩ ስፋት አኳያ ሀ/ስብከቱ “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር“ 1ኛ ጢሞ. 5፡3  ተብሎ እንደተጻፈ ክብረ አረጋውያን ለማስጠበቅ ምግባረ ሰናይ ክፍል እንዲኖረው አድርጓል፡፡

የክፍሉ ራዕይ

በየአጥቢያው በር ተኮልኩለው ያሉ የአረጋውያን አካላዊና ስነልቦናዊ ፍላጎት ተሟልቶ እንዲሁም ስብዕናቸው ተጠብቆ ቀሪ ሕይወታቸውን በክብርና ባማረ ሕይወት ሲኖሩ ማየት ፡፡

 ክፍሉ የተቋቋመበት ዓላማ

  • ለአረጋውያን በያሉበት የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳትና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አጥቢያዎችን ማስተባበር፣
  • በማህበረሰብ ውስጥ ባሉበት ስፍራ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ፣
  • ስለ አረጋውያንና ችግሮቻቸው ለማስተማር የሚያስችል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት።
  • ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት አረጋውንያን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ  ማስቻል፡፡

የክፍሉ ተልዕኮ

ለአረጋውያን የተሟላ ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ አምራችና የታሪክ ማህደር መሆናቸውን ተገንዝቦ የቀደመ ክብራቸው እንዲመለስ ማስቻል፡፡

የክፍሉ አንኳር እሴቶች

  • ሀቀኝነት፣
  • ግልጽነት፣
  • ተጠያቂነት፣
  • ሰብዓዊነት
  • ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት

የክፍሉ የትኩረት አቅጣጫዎች

‘’ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን፥ ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት።’’ 1ኛ ጢሞ. 5፡27

  • የአረጋውያን የምግብ አቅርቦትን ማሻሻል
  • የአረጋውያን የግልና የአካባቢ ንጽህና እንዲጠበቅ ማድረግ
  • የአረጋውያን ምቾት ያለው መኝታ  እንዲያገኙ ሰዎችን የማስተባበር ሥራ
  • አረጋውያን የህክምና አገልግሎት  እንዲያገኙ የማስተባበር ሥራ
  • የአረጋውያን የማህበራዊና መዝናኛ አገልግሎትን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት  
  • ከአረጋውያን ጤንነትና አቅም ጋር የሚጣጣሙ አነስተኛ የዕደጥበባት ሥራዎች አንዲሰሩ ማድረግ ወዘተ ናቸው፡፡