መንፈሳዊ ፍርድ ቤት

ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ጀምሮ ሕግ የበላይ ሆኖ በምድራችን ኑሯል፡፡ መጽሐፍት ከመጻፋቸው ሕግ ከመስጠቱ በፊት ሰዎች በተሰጣቸው መለኮታዊ ጸጋ በልቦናቸው በማገናዘብ ብቻ ሕግን ሲያከብሩ ኑሯል፡፡ ይህ ዘመን ሕገ ልቦና በመባል ይታወቃል፡፡

ሕገ ልቦና

ይህ ዘመን ከአዳም እስከ ነብዩ ሙሴ የነበረው ዘመን ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩት አበው /አባቶች ህገ እግዚአብሔር በሕሊናቸው በማመዛዘን በልቦናቸው በመገንዘብ ክፋትና ጥፋትን በመተው ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመገዛት ፍጹሞ ሕገ ልቦና ሕገ እግዚአብሔርን የጠበቁበት ዘመን ነበር፡፡ በሕገ ልቦና የተሰጣቸው ሕገ እግዚአብሔር የጣሱት ደግሞ በዚሁ በህግ ልቦና ተዳኝተው ለፍርድ በቅተዋል ለዚህም ታላቅ ምሳሌ የሚሆኑት በኖህ ዘመን የነበሩት ሕዝቦችና ሰዶምና ገሞራ ዋናዎቹ ሲሆን ሕገ እግዚአብሄርን በማክበር ደግሞ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ይጠቀሳል፡፡ ኦሪ ዘፍ 6፡1-22 ዘፍ19፡1-30 ዘፍ 39፡1-21

ሕገ ኦሪት

ከነብዩ ሙሴ እስከ ሀዲስ ኪዳን የነበረው ሕግ ነው፡፡ ይህ እስራኤል ከግብፅ ነፃ መውጣት ከጀመሩበት ከኮሬብ /ደብረሲና/ ጀምሮ የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በሕገ ኦሪት ከልቦና  ህግ ተወጥቶ ወደ ሕግ ትዕዛዛዊ የተገባበት ዘመን ነበር፡፡ የዚያን ዘመን ሕጎች መጽሐፍት የተፃፉበት የህግ መምህርን የተነሱበት የምጣኔ ሀብትና፣ የማሕበራዊ፣ እንዲሁም ፓለቲካዊ የሆኑ የሀገር፣ የህዝብ፣ የመሬት፣ የንብረት የመብት ሕጎች የረቀቀበት ዘመን ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ዝነኛው የሕጎች ሁሉ ምንጭ የሆነው ከሲና ተራራ ላይ በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ተጽፎ የተገኘው ለሙሴ የተሰጠው አስርቱ /10ቱ/ ትዕዛዛት የተሰጠው በሕገ ኦሪት ነው፡፡ ዘፀ 20፡1

  1. ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ፤
  2. የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤
  3. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፤
  4. አባትህንና እናትህን አክብር፤
  5. አትግደል፤
  6. አትስረቅ፤
  7. በሐሰት አትመስክር፤
  8. ለጣዖት አትስገድ፤
  9. አታመንዝር፤
  10. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፡፡ ዘጸ 20፡1-17

እነዚህ ሕጎች እስከ መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የቀጠሉ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስም ኦሪትና ነቢያትን ልፈፀም እንጂ ልሽር አልመጣሁም በማለት ሕጉን እንዳፀናው ገልፆ አስተምሯል ፡፡በብሉይ ኪዳን /በኦሪት/ የነበሩት በዓመተ ፍዳ፣ በዓመተ ኩነኔ የነበሩ ስለነበሩ ፍዳ ሞት አልነበሩም፡፡ እግኢአብሔር እውነተኛ ዳኛ ስለነበር በጥልቀት በነቢያቱ፣ በመሳፍንቱ ከዚያም በነገስታቱ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ቅዱስ ትዕዛዙን በየዘመኑ ይልክ ነበር፡፡ ፍትህ ያዛቡትን ከመገዘት ፈቀቅ ያሉትን ሕገ ኦሪት /ህገ እግዚአብሔርን/ የተጣሱትን በእውነተኛ ፈራጅነቱ ነቢያቱን ፣ መሳፍንቱን ፣ ነገስታቱን ከብዙ ማስጠንቀቂያ በግል ቀጥቶአቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ እነዚህ በእግዚአብሔር ፍቃድ ከተነሱት ነቢያትና መሳፍንት በህገ እግዚአብሔር ሲዳኙ የኖሩ ሲሆን ከሳኦል ጀምረው ያሉት ነገስታት ደግሞ ሲፈርዱ ኖረዋል፡፡ ለምሳሌ የታላቁ ንጉስ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን መጥቀስ ይቻላል፡፡