ሕያዉንከሙታንመካከልስለምንትፈልጋላችሁ?/ሉቃ. 24፡5/
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደሚነሣ ቅዱሳን ነቢያት አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ከትንቢቶቹም አንዱ (ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም፡፡ ወከመ ኃይል ወኅዳገ ወይን፡፡ ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ፡፡( /የተኛ ሰው ከእንቅልፍ እንደሚነቃ እግዚአብሔር ከሙታን ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ በኋላው በተተከለ መስቀል ጠላቱን ድል አደረገ/ /መዝ. 77፡65/
ስለ ጌታችን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም /ማቴ. 28፡1-15/ ማር. 16፡1-18/ /ሉቃ. 24፡ 1-12/ ዮሐ. 20፡ 1-18/ ይህን መሠረት በማድረግ የትንሣኤው ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጻ(ል፡፡
ትንሣኤ፡- ቃሉ ግእዝ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው፡፡ የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠው ለማርያም መግደላዊትና ለያዕቆብ እናት ማርያም፤ ለሰሎሜ እንዲሁም ለሌሎች ቅዱሳት አንስት ነው፡፡
ማርያም መግደላዊት አገሯ መግደሎን ስለሆነ በአገሯ መግደላዊት ተብላለች ሰባት አጋንንት አድረውባት ሰባት ዓይነት ኃጢአት ያሠሯት ነበር፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባቱንም አጋንንት አወጣላት፡፡ ይህን ከባድ ውለታ በማሰብ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልዳ ከላይ ከተጠቀሱት ቅዱሳት አንስት ጋር ሽቶ ይዛ ወደ መቃብሩ ሄደች ይህም በአገራቸው በእስራኤል ልማድ ነው፡፡ በእስራኤል ሰው በተቀበረ በሦስተኛው ቀን በመቃብሩ ላይ ሽቶ ያርከፈክፉበታል፡፡ ወደ መቃብሩ በደረሱ ጊዜ መቃብሩ ተከፍቶ ሁለት መላእክት ነጭ ልብስ ለብሰው አንዱ መልአክ በመቃብሩ በራስጌ ሌላው በግርጌ ሆነው ታዩአቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ፈሩ፣ መፍራታቸውን አይተው ሁለቱ መላእክት “አትፍሩ አይዟችሁ ሕያዉን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቷል በዚህ የለም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ እንደሚሰጥና እንደሚሰቀል፣ በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ አስቀድሞ በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደተናገረ አስቡ፡፡
መነሣቱንም ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ፈጥናችሁ ንገሯቸው” በማለት ሁለቱ መላእክት አጽናንተዋቸዋል፡፡ እነርሱም ሄደው መነሣቱን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረዋል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራ 20፡ ቁ. 19-31 እንደተጻፈው በትንሣኤ ዕለት ማታ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለፈሩ በዝግ ቤት ተሰብስበው ሳሉ የሰላም ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፡፡ ተሰብስበው በነበሩበት ቤት ገባ፡፡ በመካከላቸው ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው፡፡ እነርሱም በጣም ደስ አላቸው፡፡ እርሱም ዳግመኛ ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል የያዛችሁባቸው ግን ይያዝባቸዋል አላቸው፡፡ ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ በዚሁ ቀን አልነበረም ሌሎች ደቀ መዛሙርት ጌታን አይተነዋል አሉት፡፡ እርሱ ግን የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላኖርሁ አላምንም አላቸው፡፡
ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ ደጆችም ተዘግተው ሳሉ የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ቶማስን ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን አለው፡፡ ቶማስም ጌታዬ፤ አምላኬም ብሎ መለሰለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቶማስን ስለአየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡ ይህ ቀን ጌታችን ለሁለተኛ ጊዜ ቶማስ ባለበት ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠበት ቀን ስለሆነ ዳግም ትንሣኤ ተብሏል፡፡
የጌታችን ትንሣኤ ለክርስትናው ትምህርት መሠረት ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ የእኛም ትንሣኤ ነው፡፡ ለምን፡- በእርሱ ትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ተረጋግጧልና እኛ ሞተን ፈርሰን በስብሰን አንቀርም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእኛን ትንሣኤ በዘርዕ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ ይህም “አንተ ሰነፍ አንተ የምትዘራው እንኳን ካልፈረሰ አይበቅልም” /1ኛ. ቆሮ. 15፡36/ ይህም ማለት አንድ ገበሬ ዘርዕ ይዘራል፤ ያ ዘርዕ ከአፈር ጋር ይቀላቀላል፤ ይፈርሳል ከዚያም ይበቅላል እኛም ሞተን ፈርሰን በስብሰን አንቀርም እንነሳለን፡፡ መቃብራችን ላይ መስቀል መደረጉ የትንሣኤያችን ምልክት ነው፡፡
ስለዚህ ለእኛ ትንሣኤ መሠረቱ የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሁላችንም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን፡፡ ከዚያም በሕይወተ ሥጋ ሳሉ መልካም የሠሩ ተመስግነው ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ክፉ የሠሩ ደግሞ ተወቅሰው ዘለዓለማዊ ፍዳ ወዳለበት ወደ ገሃነመ እሳት ይገባሉ፡፡ ይህንንም ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “ስለዚህ ነገር አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሙታን ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ሰዓት ትመጣለች ሕጉን የፈጸሙ በሕይወት ለመኖር ይነሣሉ፡፡ ክፉ ሥራ የሠሩ ግን በፍዳና በጨለማ ለመኖር ይነሣሉ፡፡” /ዮሐ. 5፡29/
በዚህ መሠረት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ትንሣኤ ልቡና ያስፈልገናል፤ ትንሣኤ ልቡና ማለትም የልብ መነሣት ማለት ነው፤ ልባችን መልካም ሥራ ለመሥራት መነሣት አለበት፡፡ ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል” /ኤፌ. 5፡14/
መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃነ ረድኤትህን ላክ) ብሎ በተናገረው መሠረት ፈጣሪያችን ብርሃነ ረድኤቱን እንዲልክልን ትንሣኤውን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ለመንፈሳዊ ጉዞ መሠረቱ እምነት ነውና፡፡ እምነተ ጠንካሮች መሆን እንደሚገባን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል” /ማቴ. 17፡20/ ይህንን ሊቃውንት ሲያመሰጥሩት በሰናፍጭ ፍሬ ላይ ትንሽ እንኳን የመሰንጠቅ ምልክት አይታይም በእምነታችሁ ትንሽ እንኳን ጥርጥር እንዳይኖር፣ ጥርጥርን አስወግዳችሁ ፍጹም እምነትን ገንዘብ ካደረጋችሁ ተራራ ታፈልሳላችሁ፡፡ እንዲሁም በተራራ የተመሰለው ሰይጣንን ታወጣላችሁ ማለት ነው፡፡
እምነታችንን ደግሞ በሥራ መግለጽ ያስፈልጋል ሰው በእምነት ብቻ አይድንም ከእምነት ጋር ግድ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ “እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?” /ያዕ. 2፡14/ እምነትማ ብቻ ከሆነ አጋንንትም ያምናሉ፣ ይንቀጠቀጡማል፡፡ /ያዕ. 2፡19/
ቅዱስ ያዕቆብ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 26 ላይ በእምነት ብቻ መዳን እንደማይቻል እጅግ በሚያስደንቅ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ ይህም፡- “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡”
በዚህ መሠረት ከመከራ ሥጋ፣ ከመከራ ነፍስ እንድንድን፤ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ እምነታችንን በሥራ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡
እምነታችንን በሥራ ገልጸን ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፡፡
ለብርሃነ ትንሣኤው ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ዕርገቱ በሰላም ያድርሰን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ስርጭት ኃላፊ