የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡
በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው»
በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡
ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ሕዝብ በጎ ፈቃድ እና አርቆ አስተዋይነት ወደ እስክንድርያ ተልእኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመርያው ጳጳስ ፍሬምናጦስ ሀገረ ስብከት «ጳጳስ ዘአኩስም ወዘኩላ ኢትዮጵያ» የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው መጥተው ስለነበር ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከት እንደነበራት ይጠቁማል፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1438 ዓም ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ከግብጹ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛ ተሾመው መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ለአምሐራ፣ አቡነ ገብርኤልም ለሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተመደቡ፡፡ ይህም በወቅቱ የነበረውን የሀገረ ስብከት አደረጃጀት ያመለክታል፡፡
በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አራት ጳጳሳት ከግብጽ መጥተው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ የጎጃም፣ አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አበው በውል የተለየ ቦታ ተከልሎ ተሰጥቷቸው እንደነበር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት «ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ» በተባለው መጽሐፋቸው የአቡነ ማቴዎስን ሀገረ ስብከት ሲዘረዝሩ «ሸዋን ከበሽሎ ወዲህ መደብ አድርገው የጁን፣ ዋድላን፣ ደላንታን፣ ዳውንትን፣ ግራ መቄትን፣ ከበጌምድር መጃን፣ ስዲን፣ ፎገራን፣ ጭህራን፣ደምቢያን፣ አርማጭሆን፣ መረባን፣ ጃን ፈቀራን፣ ጃንዋራን፣ ቆላ ወገራን፣ ጠገዴን፣ ወልቃይትን» እያለ ይዘረዝራል፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያዎቹን ጳጳሳት ስታገኝ የታወጀው ዐዋጅ ዐንቀጽ አንድ «የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይስሐቅ ይሁን» ይላል፡፡ ይኼው ዐዋጅ የየአንዳንዱን ጳጳስ የሀገረ ስብከት ክልል ዝርዝር እና የመንበረ ጵጵስናውን ማረፊያ ከተማ ይተነትናል፡፡
በጣልያን ዘመን ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እና ጳጳሳት ተሰባስበው ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ሊቀ ጳጳስ አድርገው አምስት ጳጳሳትን ሲሾሙ አዳዲስ አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ አቡነ ዮሐንስ የሸዋ፣ አቡነ ማርቆስ የኤርትራ፣ አቡነ ማቴዎስ የወሎ፣ አቡነ ገብርኤል የጎንደር እንዲሁም አቡነ ሉቃስ የወለጋ አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ሆነው ተሾመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመሥረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ነበር፡፡ በ1943 ዓም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ታዴዎስን ለጎሬ፣ አቡነ ገብርኤልን ለወሎ፣ አቡነ ማርቆስን ለኤርትራ፣ አቡነ ፊልጶስን ለኢየሩሳሌም፣ አቡነ ጎርጎርዮስን ለከፋ ጳጳሳት አድርገው ሾመው ነበር፡፡ ይህም አዳዲስ አህጉረ ስብከት መመሥረታቸውን ያመለክታል፡፡ በ1948 ዓ.ም ትግራይ በሀገረ ስብከትነት ተቋቁሞ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾመውበታል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከት ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቶ፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት፣ በ1974 ዓ.ም የአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ወደ አሥራ ዘጠኋ ያህል ደርሶ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም» የተሰኘው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍ እንደሚገልጠው አርባ በሀገር ውስጥ፣ ስምንት ከሀገር ውጭ፤ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት ይገኛሉ፡፡